ባለፉት አስር ወራት 301 ሺህ ዜጎች በህጋዊ መንገድ ወደውጭ ሀገራት የስራ ስምሪት አድርገዋል - ኢዜአ አማርኛ
ባለፉት አስር ወራት 301 ሺህ ዜጎች በህጋዊ መንገድ ወደውጭ ሀገራት የስራ ስምሪት አድርገዋል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 9/2016(ኢዜአ)፦ባለፉት አስር ወራት 301 ሺህ ዜጎች ክብርና ደህንነታቸውን በጠበቀ መልኩ ወደ ውጭ ሀገራት የስራ ስምሪት ማድረጋቸውን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል የተያዘውን በጀት ዓመት ያለፉትን ዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም አስመልክቶ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት መጀመሪያ የዘርፉ ባለድርሻ አካላትን በማካተት "ዓመተ-ምርታማነት" በሚል ስያሜ እያንዳንዱ ሥራዎች ወደ ውጤት መቀየር አለበት የሚል እሳቤ ተይዞ ወደ ሥራ መገባቱን ገልፀዋል።
የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት ሰፊ ሪፎርም እየተከናወነበት ያለ ዘርፍ መሆኑን ገልጸው፤ በዚህም መንግስት በግልጽ ያስቀመጠው የዜጎች የክብር ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።
በዚህም አንደኛው የዜጎችን እንግልት መቀነስ እና አገልግሎቱን በቴክኖሎጂ የተደገፈ ማድረግ መሆኑንን አመላክተዋል።
እንዲሁም ተጓዦች ወደማያውቁት ሀገር የሚሄዱ በመሆናቸው እንዲሰለጥኑና በቂ የስነ- ልቦና ዝግጅት እንዲኖራቸው መደረጉን አመልክተዋል።
ይህ በጣም ትንሹ የሞራል ግዴታ መሆኑን ገልጸው፤ መንግስት የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ መንግስታዊ ግዴታውን እየተወጣ መሆኑን አንስተዋል።
ይሁን እንጂ ትክክለኛ ያልሆነ መረጃ ከመስጠት ጀምሮ በህገ-ወጥ መንገድ ወደውጭ ሀገራት በመላክ የሚሳተፉ አካላት መኖራቸውን ተናግረዋል።
ሂደቱ ሙሉ በሙሉ በአሰሪው መሆኑንና ለክፍያ የሚጠየቁትም የፓስፖርት እና የጤና ምርመራ መሆኑን አንስተዋል።
ከዚህ ውጪ ያሉ ክፍያዎች ህገ-ወጥ መሆናቸውን እና በዚህ ድርጊት የሚሳተፉ በሰው ህይወት መጫወት መሆኑን ተገንዝበው ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።
አሁን ላይ እየተተገበረ ባለው ቴክኖሎጂ የትኛውም በውጭ ሀገር ያለ ዜጋ የት እንዳለ ችግር ቢያጋጥማቸውም በአንድ ጥሪ ወደ ኤምባሲ መልዕክት የሚያስተላልፉበት መሆኑን ጠቁመዋል።
ቴክኖሎጂው በሁሉም የውጭ የስራ ስምሪት የሚያደርጉ ዜጎች ተደራሽ እንዲሆን ከኢትዮ-ቴሌኮም ጋር ስማርት ስልኮች የሚያገኙበት አሰራር እንዲኖር ውይይቶች እየተደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
ባለፉት አስር ወራት 301 ሺህ ዜጎች ወደ ውጭ ሀገራት የስራ ስምሪት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ከቁጥሩ በላይም ትልቁ ነገር ክብራቸው እና ደህንነታቸው በተጠበቀ መንገድ ጉዞ ማድረጋቸው መሆኑን አመላክተዋል።
በተቀባይ ሀገራትም ተቀባይ ኖሯቸው ያለምንም መጉላላት ወደ ስራቸው የሚገቡበት አግባብ መፈጠሩን ገልጸዋል።
ከተለያዩ ሀገራት ጋር አዳዲስ መዳረሻዎችን ለመክፈት እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ በተያዘው በጀት ዓመት ከሶስት ሀገራት ጋር ስምምነት ማድረግ የሚያስችሉ ውይይቶች መደረጋቸውን ተናግረዋል።
አሁንም የሚደረጉ ድርድሮች የዜጎችን መብትና ጥቅም ያስጠበቁ መሆኑን አመላክተዋል።