ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ ይደረጋሉ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 9/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ25ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።

ሀምበሪቾ ከባህር ዳር ከተማ ከቀኑ 10 ሰዓት በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።

በፕሪሚየር ሊጉ እስከ አሁን 1 ጨዋታ ብቻ ያሸነፈው ሀምበሪቾ በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች በ4ቱ ሲሸነፍ በአንዱ አቻ ወጥቷል።

በአነዚህ 5 ጨዋታዎች 3 ግቦችን ሲያስቆጥር 12 ጎሎች ተቆጥረውበታል በአሰልጣኝ ብሩክ ሲሳይ የሚመራው ሀምበሪቾ በ8 ነጥብ የመጨረሻውን 16ኛ ደረጃ ይዟል።

ተጋጣሚው ባህር ዳር ከተማ ባለፉት 5 የሊግ ጨዋታዎች ሽንፈት አላስተናገደም፤ 2 ጊዜ ሲያሸንፍ 3 ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል።

በ5ቱ ጨዋታዎች 4 ግቦችን ከመረብ ሲያሳርፍ 2 ጎሎች ተቆጥረውበታል፤ በደግአረገ ይግዛው የሚሰለጥነው ባህር ዳር ከተማ በ41 ነጥብ 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ያደረጉት ጨዋታ ያለ ምንም ግብ በአቻ ውጤት መጠናቀቁ የሚታወስ ነው።

ሌላኛው የ25ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ድሬዳዋ ከተማ እና ኢትዮጵያ መድንን ከምሽቱ 12 ሰዓት ያገናኛል።

በኮማንደር ሽመልስ አበበ የሚመራው ድሬዳዋ ከተማ ካለፉት 5 የሊግ ጨዋታዎች 2 ጊዜ ሲያሸንፍ 1 ጊዜ ተሸንፎ 2 ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።

ድሬዳዋ በእነዚህ 5 ጨዋታዎች 5 ግቦችን ሲያስቆጥር 4 ጎሎች ተቆጥረውበት በ34 ነጥብ 9ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ተጋጣሚው ኢትዮጵያ መድን በበኩሉ በሊጉ ካደረጋቸው ያለፉት 5 ተከታታይ ጨዋታዎች 4ቱን ሲያሸንፍ 1 ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል።

በ5ቱ ጨዋታዎች 8 ግቦችን ሲያስቆጥር የተቆጠረበት 1 ጎል ብቻ ነው።

በገብረመድህን ኃይሌ የሚሰለጥነው ኢትዮጵያ መድን በ28 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማ 2 ለ 1 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

በተያያዘም ትናንት በተደረጉ የ25ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወላይታ ድቻን 5 ለ 0 እንዲሁም ፋሲል ከነማ ወልቂጤ ከተማን 1 ለ 0 አሸንፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም