ቀጥታ፡

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን እና የአዘርባጃን የቤት ልማት ኤጀንሲ በጋራ ለመስራት ተስማሙ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 9/2016(ኢዜአ)፦ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን እና የአዘርባጃን የቤት ልማት ኤጀንሲ በቤት ልማት ዙሪያ በጋራ ለመስራት ተስማሙ፡፡

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የተመራው እና የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ረሻድ ከማልን ያካተተው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የልዑካን ቡድን በቤት ልማት ዙሪያ ባካሄደው ምክክር የአዘርባጃን የቤት ልማት ኤጂንሲ እና የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በጋራ ለመስራት በአዘርባጃን ዋና ከተማ ባኩ ስምምነት ላይ ደርሰዋል ፡፡

ፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ረሻድ ከማል ከአዘርባጃን የቤት ልማት ኤጀንሲ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር ሰፊ ውይይት አድርገዋል፡፡

የአዘርባጃን የቤት ልማት ኤጂንሲ በመንግስት መነሻ የኢንቨስትመንት ፋይናንስ ድጋፍ ተደርጎለት የሚገነባቸውን ቤቶች ከ 30 በመቶ እስከ 40 በመቶ ከገበያው የዋጋ ቅናሽ ያላቸውን ቤቶች ለአገሪቱ ዜጎች በሽያጭ እያቀረበ ገበያ የማረጋጋት ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝም ተጠቅሷል፡፡ 


 

የአዘርባጃን የቤት ልማት ኤጂንሲ ከመንግስት የሚያገኘውን መነሻ የኢንቨስትመንት ፋይናንስ ድጋፍ ሙሉ በሙሉ ገበያ ለመረጋጋት ለሚገነባቸው ቤቶች ግንባታ ያውላል።

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ከቅረብ ጊዜ ወዲህ የሪል ስቴት ገበያውን ለማረጋጋት እያደረገ ላለው ጥረት የአዘርባጃን የቤት ልማት ኤጂንሲ ያለውን ሰፊ ልምድ ለፌዴራል ቤቶች የሚጋራ ይሆናል፡፡ 

ሁለቱ ተቋማት በቤት ልማት ዙሪያ በትብብር ለመስራት የሚያስችላቸውን ጉዳዮች ላይ ስምምነት በመደረሱ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የአዘርባጃን የቤት ልማት ኤጀንሲን ልምድና ተሞክሮ በኢትዮጵያ ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚሰራ መገለጹን ከፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ 

የቀደሞው ኪራይ ቤቶች የአሁኑ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ራሱን ጠንካራ መንግስታዊ የሪል ስቴት ካምፓኒ ለመሆን በሚያስችለው አግባብ እየሰራ መሆኑ ተገልጿል።


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም