ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የተንጸባረቀው ሀሳብ በትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሰረተ አይደለም - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 8/2016(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የተንጸባረቀው ሀሳብ በትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሰረተ አይደለም ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር በትናንትናው ዕለት ያደረጉት ንግግር በተረጋገጠ መረጃ ላይ ያልተመሰረተና በምርጫ ወደ ስልጣን የመጣን መንግስት እንጥላለን በሚል የሚንቀሳቀሱ፣ ንጹሃንን ከሚያግቱና ከሚያሸብሩ አካላት ጋር መንግስትን መጥቀሳቸው ተገቢ አለመሆኑን አስታውቋል፡፡

የአምባሳደሩ ንግግር የኢትዮጵያ መንግስት ሀገሪቷን እንዴት መምራት እንዳለበት ያልተጠየቀ ምክር ለመምከር የሞከረ ነው ሲልም ገልጿል፡፡

የአምባሳደሩ መልዕክት ከሁለቱ ሀገራት ታሪካዊና ወዳጅነት ላይ ከተመሰረተው ግንኙነት የተቃረነ እንደሆነም ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።

ኢትዮጵያና አሜሪካ ግንኙነታቸውን አጠናክረው በመቀጠል በብሔራዊ፣ ቀጣናዊና የጋራ በሆኑ ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ እንደሚሰሩ ጠቅሶ ኢትዮጵያ የሰላምና የጸጥታ ጉዳዮችን ጨምሮ ከአሜሪካ ጋር ለመስራት ያላትን ዝግጁነት ገልጿል።

በአዲስ አበባ ከሚገኘው ኤምባሲ ጋር በመስራት የተፈጠረውን ስህተት እንዲታረም የሚያደርግ መሆኑንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

ኢትዮጵያ በመከባበር ላይ የተመሰረተ የሁለትዮሽ ግንኙነትና ትብብር እንዲኖር ቁርጠኛ መሆኗንም መግለጫው አረጋግጧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም