ቀጥታ፡

በባህር ዳር ከተማ የአምራች ኢንዱስትሪውን ምርታማነት ለማሳደግ ድጋፍ  እየተደረገ ነው

ባህር ዳር፤ ግንቦት 8/2016 (ኢዜአ)፦ በባህር ዳር ከተማ የአምራች ኢንዱስትሪውን  ዘርፍ  የማምረት አቅም  ለማሳደግ ድጋፍ   እየተደረገ መሆኑን  የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ገለጹ። 

 “ኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት“ በሚል መሪ ሃሳብ የተዘጋጀ የውይይት መድረክ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል።

በዚህ ወቅት የከተማው አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳላማው ፤ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ለምርታማነት እድገት ክፍተት የፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት የተጠናከረ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም  የብድር፣ የሃይልና ሌሎችንም የመሰረተ ልማት አቅርቦት ችግሮችን በመፍታት አምራች ኢንዱስትሪዎች የታለመላቸውን ግብ እንዲመቱ እየተደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

ኢንዱስትሪዎች ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት የተጀመረው የ“ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ እንዲሳካ  ክትትልና ድጋፍ  በማድረግ አስተዳደሩ የበኩሉን እየተወጣ እንደሚገኝም  አመልክተዋል።

በከተማ አስተዳደሩ የሚሰሩበት መሬት ከተላለፈላቸው ባለሃብቶች ውስጥ  197 ወደ ማምረት መግባታቸውን ጠቅሰዋል።

እንዲሁም ግንባታቸውን አጠናቀው ወደ ስራ ለመግባት የተዘጋጁ 217 ባለሃብቶች መኖራቸውን ያመለከቱት   አቶ ጎሹ ፤  ባለሀብቶች የወሰዱትን መሬት በአግባቡ ለታለመለት ዓላማ ማዋል እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በአማራ ክልል ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሃላፊ አቶ እንድሪስ አብዱ ናቸው።


 

አምራች ኢንዱስትሪውን ለማስፋፋትም  በሦስት ሺህ 300 ሄክታር መሬት ላይ 28 የኢንዱስትሪ መንደሮችን በማልማት ለስራ ምቹ ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል።

የኢንዱስትሪ ዘርፍ  ችግሮችን በመፍታት ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

የ “የኢትዮጵያ ታምርት” አገራዊ የንቅናቄ ግቡን እንዲመታ ክልሉ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመደገፍ እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

በክልሉ በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት በተደረጉ የንቅናቄ  መድረኮች ተስፋ ሰጪ ለውጦች መምጣታቸውን  አብራርተዋል።

በውይይቱ ላይ የክልሉና የከተማ አስተዳደሩ የአመራር አባላት ፣ ባለሀቶችና ባለድርሻ አካላት የተሳተፉ ሲሆን፤ ባለሃብቶቹ የኢንዱስትሪ ምርቶቻቸውን የሚመለከት ዝግጅት አቅርበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም