የብሪክስ ጥምረት ኢትዮጵያ በዓለም የዲፕሎማሲ ግንኙነት ዕድሎችን እንድታሰፋና ኢኮኖሚያዊ ትብብሯን እንድታሳድግ ይረዳል - አምባሳደር ዲና ሙፍቲ - ኢዜአ አማርኛ
የብሪክስ ጥምረት ኢትዮጵያ በዓለም የዲፕሎማሲ ግንኙነት ዕድሎችን እንድታሰፋና ኢኮኖሚያዊ ትብብሯን እንድታሳድግ ይረዳል - አምባሳደር ዲና ሙፍቲ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 8/2016(ኢዜአ)፦ የብሪክስ ጥምረት ኢትዮጵያ በዓለም የዲፕሎማሲ ግንኙነት ዕድሎችን እንድታሰፋና ኢኮኖሚያዊ ትብብሯን እንድታጠናመክር ያደርጋል ሲሉ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለጹ።
በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት የደቡብ ደቡብ ትብብርን በማስተዋወቅ ኢትዮጵያ በብሪክስ አባልነት የሚኖራትን ሚና፣ ዕድልና ቀጣይ ስራ የሚዳስስ የምክክር መድረክ ተካሂዷል።
አምባሳደር ዲና እንዳሉት፥ ኢትዮጵያ በብሪክስ አባልነት በንግድ፣ ቱሪዝም፣ የገንዘብ ድጋፍ፣ ቴክኖሎጂና መሰል መስኮች በሚኖራት ተጠቃሚነት ላይ ምክክር ተደርጓል።
የኢትዮጵያን የብሪክስ ጥምረት ተጠቃሚነት ለማስጠበቅም የውስጥና የውጭ ጫናዎችን መቋቋም የሚያስችል የአሰራር መርሆችን መከተል ያሰፈልጋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በብሪክስ የትብብር ጥምረት ጠንካራ አባል ሆና ለመዝለቅ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ እንደሚያስፈልጋት ምክረ ሃሳብ መቅረቡን ተናግረዋል።
የብሪክስ ጥምረት የዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ የግንኙነት ዕድሎችን በማስፋት በትብብር የተመሰረተ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ለማሳለጥ እንደሚያስችልም አመላክተዋል።
ግዙፍ የኢኮኖሚ አቅም ባለቤት የሆኑት ሩሲያ፣ ቻይና፣ ህንድና ብራዚል በማደግ ላይ ለሚገኙ ሀገራት ብዝሃ የኢኮኖሚ መስኮች መነቃቃት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
ነባርና በአዲስ መልክ ጥምረቱን የተቀላቀሉ ሀገራት ከኢትዮጵያ ጋር በመርህ ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ስላላቸው ሀገራችን የብሪክስ አዲስ የልማት ባንክን ጨምሮ የፋይናንስ ድጋፍ እንደሚስገኝላት ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን በዚሁ ጊዜ፤ ብሪክስ በዘመናዊ ዓለም ውስጥ ከፍተኛ ተቀባይነትና ተሰሚነት ያለው የትብብር ጥምረት ነው ብለዋል።
በዚህ ዓመት በተካሄደው የጥምረቱ የመሪዎች ጉባኤ ኢትዮጵያን ጨምሮ አዳዲስ ሀገራት ጥምረቱን መቀላቀላቸውና የአባልነት ጥያቄ ያቀረቡ ሀገራት መኖራቸውን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያም ጥምረቱን መቀላቀሏ የኢትዮ-ሩሲያን የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲያዊ ትብብር በማጠናከር ትልቅ ቦታ የሚሰጠው እንደሆነ ጠቁመዋል።
ጥምረቱ ሁለገብ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ዲፕሎማሲያዊና ማህበራዊ ትብብርን ለማሳደግ መሳሪያ ሆኖ ያገለግላል ብለዋል።
ሩሲያም የወቅቱ የብሪክስ ጥምረት የ2024 መሪ ሀገር መሆኗን ተከትሎ ቀጣይ ለምታስተናግደው ጉባኤ የሀገራትን ትብብር ማሳደግ የሚያስችሉ ሁነቶችን እያዘጋጀች መሆኗን አስታውቀዋል።
በመድረኩ ላይ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ ተማሪዎችና ሌሎች አካላት ተሳትፈዋል።