ኢትዮጵያና ቻይና በግብርና እና በማዕድን ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር ይሰራሉ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያና ቻይና በግብርና እና በማዕድን ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር ይሰራሉ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 8/2016(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያና ቻይና በግብርና እና በማዕድን ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ገለጹ።
የሁለቱን ሀገራት የግብርና እና የማዕድን ዘርፍ ትብብርን ማጠናከርን ዓላማ ያደረገ እና 36 የቻይና ኩባንያዎች እንዲሁም የኢትዮጵያ ባለሀብቶች የተሳተፉበት ውይይት ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ የቻንግሻ ከተማ የንግድ ቢሮ እና የኢትዮጵያ ወጣት ስራ ፈጣሪዎች ያዘጋጁት ይህ መድረክ የሀገራቱን የንግድ ማህበረሰብ ማስተሳሰርን ያለመ ነው ተብሏል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምስራቅ፣ የእስያ ፓስፊክ ሀገራት ጉዳዮች ምክትል ዳይሬክተር ጀኔራል አምባሳደር ንጉስ ከበደ እንዳሉት፥ መድረኩ ሀገራቱ በግብርና እና ማዕድን ዘርፍ ያላቸውን ትስስር ይበልጥ ለማጠናከር ያስችላል።
ኢትዮጵያና ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን በሁኔታዎች ወደ ማይቀየር ስትራቴጂካዊ አጋርነት ከፍ ማድረጋቸውን ጠቅሰው፥ ዘርፈ ብዙ የሁለትዮሽ የትብብር ስምምነቶችን ተፈራርመው እየሰሩ መሆኑን አውስተዋል።
የዛሬው ውይይትም በሁለቱ ሀገራት መካከል ለረጅም ዘመን በመተማመን የዘለቀውን እና በተምሳሌትነት የሚወሰደውን ወዳጅነት ዘላቂ የሚያደርጉ የጋራ ዕድሎችን እና የትብብር መስኮችን የሚያሰፋ ነው ብለዋል።
በባለሀብቶች መካከል እንዲሁም በመንግስትና በንግዱ ማህበረሰብ መካከል ትስስር መኖሩ በዲፕሎማሲው መስክ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማሳደግ ወሳኝ እንደሆነም ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ የንግድና ኢኮኖሚ ዘርፍ ሃላፊ ያንግ ዪሃንግ በበኩላቸው፥ ቻይና በግብርና እና በማዕድን ዘርፍ ያላትን ልምድና እውቀት ለኢትዮጵያ ለማካፈል ዝግጁ ናት ብለዋል።
የኢትዮጵያ የማዕድን እና የግብርና ምርቶች በቻይና ሰፊ የገበያ ዕድል እንዲያገኙ ሀገራቸው ከዘርፉ አምራቾች ጋር በቅርበት ለመስራት ቁርጠኛ እንደሆነች አረጋግጠዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አክሊሉ ታደሰ እንዳሉት፥ በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለባለሀብቶች የተሳለጠና የተቀናጀ አገልግሎት እየተሰጠ ነው፡፡
መንግስት ለውጭ ባለሀብቶች ዝግ ሆነው የቆዩ የንግድና የኢንቨስትመንት ዘርፎችን ክፍት የሚያደርግ ውሳኔ ማሳለፉን ገልጸው፥ በዚህም የቻይና ባለሃብቶች ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ አስረድተዋል፡፡
አያይዘውም በግብር፣ ማዕድንና በሌሎች የኢንቨስትመንት ዘርፎች የቻይና ኩባንያዎች እንዲሰማሩ ጥሪ አቅርበዋል።