የብዝሃ ህይወት ሀብቶችን ለሀገርና ህዝብ ጥቅም ለማዋል የዘርፉ ተዋንያን በቅንጅት መስራት አለባቸው - ግብርና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የብዝሃ ህይወት ሀብቶችን ለሀገርና ህዝብ ጥቅም ለማዋል የዘርፉ ተዋንያን በቅንጅት መስራት አለባቸው - ግብርና ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 8/2016(ኢዜአ)፦የብዝሃ ህይወት ሀብቶችን ለሀገርና ህዝብ ጥቅም ለማዋል የዘርፉ ተዋንያን በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት ዓለም አቀፍ የብዝሃ ህይወት ቀንን "የእቅዱ አካል እንሁን" በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ መርሃ ግብሮች እያከበረ ነው፡፡
ኢንስቲትዩቱ የሚያከናውናቸውን ስራዎች የሚያሳይ አውደ ርዕይ የተከፈተ ሲሆን የፓናል ውይይትና ሌሎች መርሃ ግብሮችም እስከ ግንቦት 22 ቀን 2016 ዓ.ም ይቀጥላሉ፡፡
የግብርና ሚኒስትር የተፈጥሮ ሀብት ዘርፍ አማካሪ ታረቀኝ ፅጌ እንዳሉት፤ ብዝሃ ህይወት ሥነ ምህዳርን ለማስቀጠል፣ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ፣ ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለማፋጠንና የአየር ንብረት ለውጥ ለመቋቋም የጎላ አበርክቶ አለው፡፡
ብዝሃ ህይወትን ማንበርና የምድርን ከባቢ መጠበቅ እንዲሁም ዘላቂነትን ማረጋገጥ ለቀጣዩ ትውልድ የተጠበቀችና የለማች አገር ማስረከብ ነው ብለዋል።
ኢንስቲትዩቱ የብዝሃ ህይወት ሀብቶችን ለመጠበቅ ያከናወናቸው ተግባራትና የተገኙ ውጤቶች የሚበረታቱ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ያላትን የብዝሃ ህይወት ሀብቶች ጥቅም ላይ ለማዋል የተተገበሩ የልማት ስራዎች በቂ እንዳልሆኑ አንስተዋል፡፡
በመሆኑም ሀገር ከብዝሃ ህይወት ሀብት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ የዘርፉ ተዋንያን ከመንግስት ጋር በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ አስረደተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መለሰ ማሪዮ በበኩላቸው፤ የብዝሃ ህይወት ሀብቶቻችንን ለመጠበቅና ለማንበር የተለያዩ ተግባራትን እያከናወንን ነው ብለዋል።
በዚህም 7 የብዝሃ ህይወት ማዕከላት፣ 3 የዕፅዋት አፀዶች፣ ከ30 በላይ የማህበረሰብ ዘረመል ባንኮች እና 28 የደን ዘረመል ባንኮችን በማቋቋም የብዝሃ ህይወት ሀብቶች እየጠበቁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ዓለም አቀፉ የብዝሃ ህይወት ቀንም የብዝሃ ህይወት ሀብት ጥበቃ ፖሊሲ አውጭዎች እና ማህበረሰቡን በማስገንዘብ መልካም ተሞክሮዎችን ለመቀመር እድል ይፈጥራል ነው ያሉት፡፡