"የዓይን ብሌን" ከስጦታዎች ሁሉ የላቀ ስጦታ

በዓይን ብሌን ጠባሳ ብርሃኑን ያጣ ሰው ዳግም ዕይታውን ለማግኘት  ሰዎች  ከህልፈተ-ሕይወታቸው በኋላ  የዓይን ብሌናቸውን በበጎ ፈቃደኞች  ለመለገስ ቃል በገቡት መሰረት   ገቢራዊ ሲደረግ ነው።

በኢትዮጵያም የበጎ ፈቃደኞች የዓይን ብሌን ልገሳ ከተጀመረ ዓመታትን አስቆጥሯል፤ ብዙዎቹም ዓይን ብሌናቸውን በመለገስ ሰዎችን  ባለ ብርሃን አድርገዋል። 

ከእነዚህ  በጎ ፈቃደኖች መካከል ኢዜአ   ስምረት ተሾመ እና  ነጋ ደምሴን   ለአብነት አነጋግሯል።

በጎፈቃደኞቹ ይህን ተግባር ሲያስረዱም  የዓይን ብሌን ለመለገስ ቃል መግባት  የዓይንን ብርሃኑን ያጣ ሰው ዳግም ዕይታውን ማግኘት እንዲችል ማድረግ ነው ።

"የዓይን ብሌን መለገስ ለእኔ ምንም አያጎድልብኝም" የምትለን  ስምረት ተሾመ እንዲያውም ባደረኩት በጎ ተግባር በፈጣሪም ሆነ  በሰው ምስጋና አገኛለሁ ትላለች።

ምድር ላይ የተሰጠኝ  ዕድሜ እስኪያልቅ  የአንድን ሰው የዓይን ብርሃን እንደምመልስ ሳስብ ዘመኔን በደስታ እኖራለሁ ብላለች።

ሌላውም እንደኔ የዓይን ብሌን ቢለግስ የእኔን  ደስታ ያጣጥማት ስትል በማከል ። 


 

ከሕይወተ ህልይወቴ በኋላ ለማደርገው  የዓይን ብሌን ልገሳ በሕይወት እያለሁ  ቃል በመግባቴ ትልቅ የህሊና ደስታ እግኝቻለሁ የሚለን ደግሞ   ሌላኛው በጎ ፈቃደኛ ነጋ ደምሴ  ነው ።


 

በጎ አድራጊዎች ባደረጉላቸው የዓይን ብሌን ልገሳ ማየት መቻላቸውን ምስክር የሚሁኑን  ወጣት መታሰቢያ ንጉሴ እና ወጣት ታሪኩ ሁሴን ናቸው። 


 

ከበጎ ፈቃደኞች በተገኘ የዓይን ብሌን ዕይታቸውን በማግኘታቸው ጤናማ ሕይወትን መምራት እንዲችሉ አድርጎናል ሲሉም  አስተያየታቸውን ይገልጻሉ።

በተደረገላቸው የዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ እንደልባቸው ተንቀሳቅሰው መማርና መሥራት መቻላቸውንም ተናግረዋል።


 

የኢትዮጵያ ደምና ሕብረ-ህዋስ ባንክ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሀብታሙ ታዬ ይህን ሲያስረግጡ ፤  በሀገራችን  በዓይን ብሌን ጠባሳ ምክንያት ዕይታቸውን ያጡ ሰዎች በሕክምና የዓይን ብርሃናቸውን ለማግኘት ወረፋ የሚጠባበቁ በርካታ ዜጎች መኖራቸውን ገልፀዋል።

የእነዚህን ሰዎች ዕይታ ለመመለስም የኅብረተሰቡን በጎ ፈቃደኝነት  የሚጠይቅ ሰብዓዊ ተግባር መሆኑን በመጠቆም ።

እንደ ሀገር ኢትዮጵያውያን ስለ ዓይን ብሌን ልገሳ ያለን ባህል ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል ቢኖሩትም ከችግሩ ስፋት አንጻር  በሚፈለገው ደረጃ ሕብረተሰቡ በቂ ባህል አጎልብቷል ማለት ያዳግታል ሲሉ።

አገልግሎቱ ሕብረተሰቡ ስለ ዓይን ብሌን ልገሳ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ለማስቻል የተለያዩ ሥራዎች በመሥራት ላይ ይገኛል ብለዋል።

የዓይን ብሌን ንቅለ-ተከላ ሕክምናን ለማግኘት የሚሹ ወገኖችን ህልማቸው እውን እንዲሆን ሕብረተሰቡ የዓይን ብሌን ለመለገስ ቃል የመግባት ባህሉን እንዲያጎለብት አቶ ሀብታሙ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል። 

ለእነዚህም ወገኖች የዓይን ብርሃናቸውን ዳግም እንዲያገኙ አገልግሎቱ የዓይን ብሌን የማሰባሰብ ሥራ እና ሕብረተሰቡን ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ በመሥራት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ተቋሙ በዓይን ብሌን ጠባሳ ምክንያት ብርሃናቸውን ላጡ ወገኖች  ዕይታቸውን ዳግም  እንዲያገኙ ባለፉት ዘጠኝ ወራት  የዓይን ብሌን የማሰባሰብ ሥራ ሲሰራ መቆየቱን ገልፀዋል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት 300 የሚሆኑ ሰዎችን የዓይን ብሌን ለመለገስ ቃል ለማስገባት እና 195 የዓይን ብሌን ለመሰብሰብ መታቀዱን አውስተዋል።

በዚህም 203 የዓይን ብሌን መሰብሰብ እንደተቻለና 288 የኅብረተሰብ ክፍሎች  የዓይን ብሌናቸውን  ለመለገስ ቃል መግባታቸውን ተናግረዋል።

በቀጣይም አገልግሎቱ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በመሥራት የዓይን ብሌን የማሰባሰብ እና የማኅበረሰቡን ግንዛቤ የሚያጎለብቱ ሥራዎች ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም