ቀጥታ፡

የኢትዮጵያና ተርኪዬን ዘርፈ ብዙ ግንኙነት የሚያጠናክር ምክክር ተካሄደ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 8/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያና ተርኪዬ መካከል ያለውን የንግድ፣ የኢንቨስትመንትና ኢኮኖሚ ግንኙነት የሚያጠናክር ምክክር ተካሄደ።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር አቶ ገብረመስቀል ጫላ ከቱርክ አምባሳደር ጋር የኢትዮጵያን እና የተርክዬን የንግድ ግንኙነት በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡

የግብርና ምርቶችን ወደ ተርክዬ በመላክ እና የግሉን ዘርፍ ግንኙነት (B2B) በማጠናከር በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድ ሚዛን ክፍተት ማጥበብ እንደሚያስፈልግ ሚኒስትሩ አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዘርፉን ለውጪ ባለሀብቶች ክፍት እያደረገች በመሆኑ የተርክዬ ባለሀብቶች መጥተው ኢንቨስት እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡


 

ተርክዬ በንግድና በኢኮኖሚ፣ በቴክኖሎጂ እና በአቅም ግንባታ ልምዷን እንድታካፍል የጠየቁት ሚኒስትሩ የተርክዬ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በንግድና ኢንቨስትመንት ለሚያደርጉት ተሳትፎ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ አመላክተዋል፡፡

የተርክዬ አምባሳደር ሚስተር በርክ ባራን በበኩላቸው ኢትዮጵያና ተርኪዬ ዘመናትን የተሻገረ የንግድና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በተርኪዬ ገበያ ቡና፣ የቆዳ ውጤቶች እና ሌሎችም የኢትዮጵያ ወጪ ንግድ ምርቶች ፍላጎት እንዳለም አስታውቀዋል፡፡

የሀገራቱን የሁለትዮሽ የንግድ ግንኙነት በእጅጉ ለማጠናከር ሁሉንም የንግድና ኢኮኖሚ ጉዳዮች በአንድ መድረክ አምጥቶ መምከር የሚያስችል የጋራ የኢኮኖሚ ኮሚሽን ለማካሄድ መስማማታቸውን ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም