ቀጥታ፡

አዲሱን የኤርፖርት ሲቲ ግንባታ ዲዛይን የሚያከናውን የአማካሪ ድርጅት መረጣ እስከ መጪው መስከረም ይጠናቀቃል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 8/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አዲሱን የኤርፖርት ሲቲ ግንባታ ለማስጀመር ዝርዝር ዲዛይኑን የሚያከናውን አማካሪ ድርጅት መረጣ እስከ መጪው መስከረም እንደሚጠናቀቅ አስታወቀ።

አየር መንገዱ በፍጥነት እያደገ የመጣውን የደንበኞቹን ቁጥር ታሳቢ በማድረግ ዘመናዊና ግዙፍ የኤርፖርት ከተማ ግንባታ እንደሚያከናውን ከ4 ዓመት በፊት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ከቢሾፍቱ ከተማ ወጣ ባለ ሥፍራ ላይ የሚገነባው ይህ ፕሮጀክት፥ የካርጎ ሎጂስቲክ ማዕከል፣ ዘመናዊ ሆቴሎችና ከቀረጥ ነጻ የተለያዩ የግብይት ስፍራዎች እንደሚኖረውም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ፕሮጀክቱ በተለያዩ ምክንያቶች በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ሳይጀመር ቆይቷል።

የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በዓመት እስከ 25 ሚሊዮን ያህል ብቻ መንገደኞችን ማስተናገድ የሚችል መሆኑን ያነሱት ዋና ስራ አስፈጻሚው፣ ሆኖም የደንበኞች ቁጥር በመጪዎቹ ጥቂት ዓመታት በእጥፍ እንደሚያድግ ይጠበቃል ብለዋል።

በመሆኑም የአየር መንገዱን እድገት እና የመንገደኞችን ቁጥር መጨመር ታሳቢ ያደረገ ግዙፍ አውሮፕላን ማረፊያ (ኤርፖርት ሲቲ) መገንባት የግድ መሆኑን በማመን ወደ ስራ መገባቱን ጠቅሰዋል።


 

ከቢሾፍቱ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኝ ስፍራ የሚገነባውን አዲሱን ፕሮጀክት ግንባታ ለመጀመርም የተለያዩ የዝግጅት ምዕራፍ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አብራርተዋል።

ለአብነትም የኤርፖርት ሲቲ ግንባታውን ዲዛይን የሚሰሩ ሁለት አማካሪ ድርጅቶችን ለመቅጠር ይፋዊ ጨረታ መውጣቱን ጠቅሰው፥ የአማካሪዎች መረጣ እስከ መጪው መስከረም እንደሚጠናቀቅ አመላክተዋል።

ፕሮጀክቱ ከዘገየባቸው ምክንያቶች አንዱ ኤርፖርት ሲቲው በሚገነባበት ቦታ የሚኖሩ አርሶ አደሮችን ሁኔታ ለማስተካከል ረጀም ጊዜ በመውሰዱ ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት አርሶ አደሮቹ ኑሯቸውን የሚመሩበትን ስራ ለመፍጠር የሚያስችል ጥናት መከናወኑን ገልጸዋል።

የአርሶ አደሮቹን ፕሮጀክት ወደ ተግባር ለማስገባትም የሚያስፈልገው የገንዘብ መጠን የታወቀ ሲሆን፥ የፕሮጀክት ዲዛይን የሚሰራ አማካሪ እየመረጥን ነው ብለዋል።

አዲስ የሚገነባው ኤርፖርት ሲቲ ለአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክና ለሞጆ ደረቅ ወደብ ቅርብ በመሆኑ ትልቅ የኢንዱስትሪያል ሎጂስቲክ ማዕከል እንደሚሆንም ተገልጿል።

የኤርፖርት ሲቲ ግንባታ ሲጠናቀቅ በዓመት 100 ሚሊዮን መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም እንዳለውም ነው የገለጹት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም