ቀጥታ፡

የብሪክስ ጥምረት የብዝኅ ኢኮኖሚ ልማትን በማስፋት  የጋራ ተጠቃሚነት እንዲፈጠር ያደርጋል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 8/2016(ኢዜአ)፦  የብሪክስ ጥምረት የብዝኅ ኢኮኖሚ ልማትን በማስፋት በትብብር ላይ ለተመሰረተ የጋራ ተጠቃሚነት እንዲፈጠር የሚያደርግ መልካም አጋጣሚ መሆኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለጹ። 

የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ የብሪክስ አባልነት የሚያስገኘውን ዕድልና ቀጣይ ስራ የሚዳስስ የምክክር መድረክ አካሂዷል። 

በመድረኩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፣ በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን፣ የዩኒቨርስቲው ምሁራን፣ ተማሪዎችና ሌሎች አካላት ተሳትፈዋል። 

በመድረኩ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ባቀረቡት የመነሻ  ጽሁፍ፥ ብሪክስ የብዝኅ ኢኮኖሚ ግንባታን በማስፋት በትብብር ላይ የተመሰረተ የጋራ ተጠቃሚነት እንዲፈጠር ያደርጋል ብለዋል። 

ብሪክስን በአባልነት የተቀላቀሉ አገራትም በሀይል፣ በጤና፣ ትምህርት፣ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ንግድ እና ኢንቨስትመንት መስኮች ልምድና ተሞክሮ እንዲጋሩ እንደሚያስችል ገልጸዋል። 

ኢትዮጵያም ባላት ስትራቴጂክ ጂኦፖለቲካና እምቅ የተፈጥሮ ጸጋ በኢንቨስትመንት ትብብር  ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ብልጽግናዋን ለማሳለጥ እንደሚያስችላት አንስተዋል። 

የብሪክስ ጥምረትም የአባል አገራቱን የጋራ ተጠቃሚነት ባከበረ  ዘርፈ ብዙ ጠንካራ ወዳጅነት ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል። 

የብሪክስ ጥምረት የኢትዮጵያን ብዝኅ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማሳለጥ መልካም አጋጣሚ መፍጠሩንም አመላክተዋል። 

በዚሁ መድረክ ላይ ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗ የሚያስገኘውን ጠቀሜታ እና  የቀጣይ የቤት ስራን የሚዳስሱ የመነሻ ጽሁፎች ቀርበው ምክክር እየተደረገባቸው ይገኛል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም