በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ሴቶች የሚያነሷቸውን አጀንዳዎች በተሟላ ሁኔታ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ሴቶች የሚያነሷቸውን አጀንዳዎች በተሟላ ሁኔታ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ገለጸ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 8/2016(ኢዜአ)፦ በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ሴቶች የሚያነሷቸውን አጀንዳዎች በተሟላ ሁኔታ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ገለጸ።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ብሌን ገብረመድህን፤ በምክክር ሂደቱ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችና አጠቃላይ የሴቶችን ተሳትፎ በተመለከተ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚያነሷቸው የተለያዩ ሃሳቦች ለኮሚሽኑ ዋነኛ ግብዓት መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በዚህ ረገድ በተለይም የሴቶች ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
በምክክር ሂደቱ እስካሁን በአሥር ክልሎችና በሁለት ከተማ መስተዳድሮች ያሉ ሁሉንም ወረዳዎች ያሳተፈ የኅብረተሰብ ተወካዮች ምርጫ ማካሄዱንም ገልፀዋል።
በክልል ደረጃ 20 የሚሆኑ ባለድርሻ አካላት ተወካዮቻቸውን እንዲለዩ መደረጉን ጠቅሰው፤ በምክክር ሂደቱ ሴቶች የሚያነሷቸውን አጀንዳዎች በተሟላ ሁኔታ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ ምክትል ሰብሳቢ እና የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የአማካሪ ቡድን አባል ራሔል ባፌ(ዶ/ር)፤ በተለይም የፖለቲካ ፓርቲዎች ሀገራዊ ምክክሩ ያለውን ጠቀሜታ የማስገንዘብ ከፍተኛ ሚና ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
በተለያዩ አጋጣሚዎች በሚከሰቱ ችግሮች በተለይም ሴቶች የችግሩ ገፈት ቀማሽ መሆናቸውን አንስተው፤ ለመፍትሔው በሚደረገው ጥረት ላይ ተሳትፏቸው መጎልበት እንዳለበት ገልፀዋል።