ቀጥታ፡

የንግድና ሰብአዊ መብት ብሔራዊ የድርጊት ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር መካሄድ ጀመረ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 8/2016(ኢዜአ)፦ ከንግድ ጋር የተያያዙ  የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ለመከላከል ያለመ ብሔራዊ የድርጊት ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።

በመድረኩ የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ ኤርሚያስ የማነብርሃን(ዶ/ር)፣ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት አበባ እምቢአለ፣ የፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል ዘላለም መንግስቴ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ምክትል ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ ኤርሚያስ የማነብርሃን (ዶ/ር) እንዳሉት፤ የተ.መ.ድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2011  መንግሥታት በንግድ አውድ ውስጥ የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃን ለማረጋገጥ የሚያስችላቸውን የተባበሩት መንግሥታት የቢዝነስ እና ሰብዓዊ መብቶች መመሪያ መርሆዎችን ማጽደቁን አንስተዋል።  

ኢትዮጵያም እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2019 የተባበሩት መንግሥታት 3ኛው ሁሉን-አቀፍ ወቅታዊ የሰብዓዊ መብት ግምገማ ላይ ያቀረበችውን ብሔራዊ ሪፖርት ተከትሎ ዜጎቻቸውን ከቢዝነስ ነክ ጎጂ የሰብአዊ መብት ተጽዕኖዎች ለመጠበቅ ተጨባጭ እርምጃ መውሰድ እንዲቻል በቢዝነስ እና ሰብዓዊ መብቶች ላይ ብሔራዊ የድርጊት መርሃ- ግብር እንድታዘጋጅ የተሰጣትን ምክረ-ሀሳብ ሙሉ በሙሉ መቀበሏ ይታወቃል።

በዚህም መሠረት የድርጊት መርሃ-ግብሩን ለማዘጋጀት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት በተለይም ከሰብዓዊ መብት ተቋማት እና ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር በመምከር የዐብይ እና የባለሙያዎች ኮሚቴዎችን ማዋቀር መቻሉን ተናግረዋል።

የሰነድ ዝግጅቱ ሥራ የሚያልፍበትን ሂደት የሚያመላክት ፍኖተ-ካርታም ተዘጋጅቶ መተግበር መጀመሩን ጠቁመዋል፡፡ 

በቀጣይም በብሔራዊ ደረጃ የመነሻ ጥናት የሚካሄድ መሆኑን ተናግረዋል።

የፍትሕ ሚኒስቴርም በማቋቋሚያ አዋጁ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የድርጊት መርሃ-ግብሩን የማዘጋጀት ሥራውን በበላይነት እየመራ፤ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ተቋማት በሙሉ ተገቢውን ተሳትፎ እንዲያደርጉ የማስተባበር ሥራውን በከፍተኛ ትኩረት እንደሚያከናውን ጠቁመዋል፡፡ 

ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮዎችን ለመቅሰምም አግባብነት ካላቸው ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በቅርበት ለመሥራት ተገቢው ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡  

በብሔራዊ የንግድ እና ሰብዓዊ መብት ድርጊት መርሃ-ግብር ዝግጅት እና ትግበራ ምዕራፎች ውስጥ ሚና ያላቸው ተቋማት በሙሉ ለዚህ ትልቅ ዓላማ ግብ መሳካት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ እና በሙሉ የባለቤትነትና የኃላፊነት ስሜት እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም