በዘንድሮው የበልግ ወቅት 63 ሚሊዬን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 8/2016(ኢዜአ)፦በዘንድሮው የበልግ ወቅት 63 ሚሊዬን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

በኢትዮጵያ የበልግ አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች የግብአትና ሌሎች አስፈላጊ አቅርቦቶችን በማሟላት የታቀደውን የምርት መጠን ለማግኘት የሚያስችል ዝግጅት መደረጉንም አመልክቷል።

የግብርና ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና ኮምዩኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ ከበደ ላቀው፤ የኢትዮጵያን የእርሻ መሬት በማስፋት፣ ድግግሞሹን በመጨመር እና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ ምርታማነትን ለመጨመር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። 

ለግብርናው ዘርፍ በሰጠው ትኩረት አርሶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች በበጋ መስኖ፣ በመኸር እርሻና በበልግ በዓመት ሁለትና ሶስት ጊዜ እየተመረተ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ለዚህም አፈር ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘርና መሰል የግብርና ግብዓቶችን በስፋት በማቅረብና በማሰራጨት የአርሶ አደሩን ፍላጎት ማሟላት ተችሏል ብለዋል፡፡


 

በተለይም የስንዴ ልማት፣ የሌማት ትሩፋትና የከተማ ግብርና በዘርፉ መሰረታዊ ለውጥና ተጨባጭ ውጤት የተገኘባቸው መሆናቸውን ገልጸዋል።

የኩታ ገጠም እርሻና ሜካናይዜሽንን ገቢራዊ ከማድረግ ባለፈ ትራክተርና መሰል ዘመናዊ የግብርና ማሽነሪዎች ለአርሶ አደሩ በስፋት እየቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል።

በተያዘው የምርት ዘመን 19 ነጥብ 4 ሚሊዬን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ተፈጽሞ፤ 12 ሚሊዬን ኩንታል ወደ ሀገር ውስጥ ገብቶ ለበጋ መስኖ ልማትና ለበልግ አብቃይ አካባቢዎች እየተሰራጨ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዘንድሮው የበልግ ወቅት 256 ሺህ ኩንታል የተለያዩ አዝርዕት ምርጥ ዘር የተሰራጨ ሲሆን 2 ነጥብ 6 ሚሊየን ሄክታር መሬት በዘር ስለመሸፈኑም ተናግረዋል።

በመሆኑም በዘንድሮው የበልግ ወቅት 63 ሚሊዬን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዷል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የአየር ትንበያ መረጃ መሰረት በበልግ አብቃይ አካባቢዎች ተመጣጣኝ ዝናብ በመኖሩ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ ቀደም ብሎ ስለመመላከቱም ጠቅሰዋል።

በመሆኑም የአብዛኛውን የኢትዮጵያ ክፍል በሚሸፍነው የመኸር ወቅት እርሻ አርሶ አደሩን በስፋት ተጠቃሚ ለማድረግ የግብርና ግብዓት ማጓጓዝና የትራክተር አቅርቦት ቅድመ ዝግጅት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የበጋ የመስኖ ስንዴ ልማትን ጨምሮ በሌሎችም የግብርና ስራዎች በምግብ ራስን ለመቻል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም በበጀት ዓመቱ የበጋ መስኖ ልማት ብቻ 3 ሚሊዬን ሄክታር መሬት በማልማት ከ87 ሚሊዬን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም