ቀጥታ፡

የገቢ መጠንን ለማሳደግ ከተለምዷዊ አሰራር የተላቀቀና ዘመኑን የሚመጥን የገቢ አሰባሰብ ስርአት መከተል ይገባል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 8/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን የገቢ መጠንን ለማሳደግ ከተለምዷዊ አሰራር የተላቀቀና ዘመኑን የሚመጥን የገቢ አሰባሰብ ስርአት መከተል ይገባል ሲሉ የብልፅግና ፓርቲ ፕሬዝዳንትና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አሳሰቡ።

የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የ2016 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ሀገራዊ የልማት፣ የሰላምና የፖለቲካ ክንውኖችን በጎርጎራ ገምግሟል።

በመድረኩ የፓርቲው ፕሬዝዳንትና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፤ በጉዳዮቹ ዙሪያ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በተለይም የገቢ ዘርፉ እያደገ መምጣቱን ካለፈው ዓመት ጋር በንፅፅር አቅርበዋል።

በ2015 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ከሁሉም የታክስ ዓይነቶችና ከቀረጥ 324 ቢሊዮን ብር የተሰበሰበ ሲሆን በ2016 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት 374 ቢሊዮን ብር መድረሱን ጠቅሰዋል።

የጋራ ገቢ በ2015 ዘጠኝ ወራት 42 ቢሊዮን ብር የነበረ ሲሆን በተመሳሳይ ወራት ዘንድሮ 54 ቢሊዮን ብር መድረሱንም ተናግረዋል።

አጠቃላይ የሚሰበሰበው ገቢ ግን ከሀገሪቱ አቅምና ፍላጎት አኳያ ዝቅተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

አሁን እየተሰበሰበ ያለው ገቢ በእጥፍ ቢያድግ ለትውልድ የሚጠቅሙ በርካታ ፕሮጀክቶችን መገንባትና የሀገርን ብልፅግና እውን ማድረግ ይቻላል ሲሉም አስረድተዋል።

የገቢ ዘርፍ ተቋማት ዘመኑን የሚመጥን የታክስ አሰባሰብና አስተዳደር ስርዓትን በመከተል የግብር ስወራና ማጭበርበርን የመግታት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።

የገቢ መጠንን ለማሳደግ ከተለምዷዊ አሰራር የተላቀቀና በቴክኖሎጂ የሚመራ ዘመኑን የሚመጥን የገቢ አሰባሰብ ስርአት መከተል ይገባል ብለዋል።

የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ፤ በለውጡ ዓመታት በፈተናዎች ውስጥም ቢሆን የሀገር ውስጥ ገቢና ቀረጥ እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።


 

በፓርቲና በመንግስት የተቀመጠውን ሀገራዊ የብልፅግና ራዕይ ለማሳካት የገቢ ዘርፉን አፈጻጸም ማሳደግ ወሳኝ መሆኑንም ተናግረዋል።

የሚሰበሰበው ገቢ እያደገ ቢመጣም ከኢትዮጵያ የመልማት አቅም እና ከሀገራዊ ምርት ያለው ድርሻ ሲታይ ውስን መሆኑ በግምገማው መነሳቱንም ጠቅሰዋል።

በመሆኑም በቀጣይ በቴክኖሎጂ የታገዘ የታክስ አሰባሰብን ማጠናከርና የታክስ አስተዳደርን ማጥበቅ እንዲሁም የታክስ መሰረትን ማብዛትና የማስፋት ስራ ይከናወናል ብለዋል።

የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴና ሕገ ወጥ ንግድን ለመቆጣጠር ዲጅታል አሰራር መዘርጋትና የድንበር አካባቢ ቁጥጥርን በማጥበቅ መስራት ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም