ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ25ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ ይጀመራል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 8/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ25ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።

ወላይታ ድቻ እና የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከቀኑ 10 ሰዓት በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት 5 ተከታታይ ጨዋታዎች 4ቱን ሲያሸንፍ 1 ጊዜ አቻ ወጥቷል።

በእነዚህ 5 ጨዋታዎች 12 ጎሎችን ሲያስቆጥር 5 ግቦችን አስተናግዶ በ50 ነጥብ በሊጉ 1ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ተጋጣሚው ወላይታ ድቻ ካለፉት 5 የሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንዱን ብቻ ሲሆን በ3ቱ ሲሸነፍ በአንዱ ነጥብ ተጋርቷል።

በያሬድ ገመቹ የሚሰለጥነው ወላይታ ድቻ በ5ቱ ጨዋታዎች 4 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 6 ጎሎች ተቆጥረውበት በ28 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያ ዙር ባደረጉት ጨዋታ ወላይታ ድቻ 1 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

በሌላኛው የ25ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ፋሲል ከነማ ከወልቂጤ ከተማ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።

ፋሲል ከነማ ካለፉት 5 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች በአንዱ ሲያሸንፍ በተመሳሳይ በአንዱ ተሸንፎ በሶስቱ አቻ ወጥቷል።

በ5ቱ ጨዋታዎች 5 ግቦችን ሲያስቆጥር በተመሳሳይ 5 ጎሎች አስተናግዶ በ37 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ተጋጣሚው ወልቂጤ ከተማ በበኩሉ በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት 5 ተከታታይ ጨዋታዎች በ4ቱ ሲሸነፍ በአንዱ ደግሞ አቻ ተለያይቷል።

በእነዚህ 5 የሊጉ ጨዋታዎች 3 ግቦችን ሲያስቆጥር 10 ግቦችን አስተናግዶ በ16 ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያ ዙር በሊጉ ባደረጉት ጨዋታ ፋሲል ከነማ 1 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

የፕሪሚየር ሊጉ የ25ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ነገም ቀጥሎ ሲውል ሀምበሪቾ ከባህር ዳር ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት፤ ድሬዳዋ ከተማ ከኢትዮጵያ መድን ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።

የሊጉ የ25ኛ ሳምንት ጨዋታዎች እስከ ግንቦት 11 ቀን 2016 ዓ.ም ይቆያሉ።

የፕሪሚየር ሊጉን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት የሃዋሳ ከተማው አጥቂ አሊ ሱሌማን በ13 ግቦች ሲመራ ምንይሉ ወንድሙ ከመቻል በ12 ግቦች ይከተላል።

የባህር ዳር ከተማው ቸርነት ጉግሳ በ11 እና የቅዱስ ጊዮርጊሱ አማኑኤል ኤርቦ በ10 ግቦች ቀጣዩን ደረጃ ይዘዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም