ቀጥታ፡

ኢንዱስትሪው የሚፈልገውን የሰው ኃይል ለማፍራት ከግሉ ዘርፍ ጋር በትብብር እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 7/2016 (ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪው የሚፈልገውን ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ኃይል ለማፍራት ከግሉ ዘርፍ ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ገለጸ።

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በክህሎት ልማት፣ በኢንዱስትሪና ትምህርት ተቋማት ትብብር የተሻለ አፈጻጸም ላሳዩ ድርጅቶች እውቅና ሰጥቷል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ በሬቻ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ኃይል ለመፍጠር ከግል ዘርፉ ጋር በትብብር እየተሰራ ነው።


 

ከሥርዓተ-ትምህርት ቀረፃ ጀምሮ በሥልጠና፣ በሙያ ብቃት ምዘና  እንዲሁም ቅጥር በመፈጸም  በትብብር እየተሰራ እንደሚገኝ ነው የገለጹት።

ለዚህም ከኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራትና ሌሎች ተቋማት ጋር በመተባበር ላለፉት ሦስት ዓመታት የሙከራ ፕሮግራም ሲተገብር መቆየቱን ተናግረዋል።

እውቅና የተሰጣቸው ተቋማት ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር  ስምምነት በመፈራረም የጋራ ዕቅድ በማውጣት በተግባር የተደገፈ ሥልጠና የሰጡና ቅጥር በመፈጸም የተሻለ አፈጻጸም ያላቸው እንደሆኑ ጠቁመዋል። 

ትብብሩ በሰው ኃይል አቅርቦትና በኢንዱስትሪው ፍላጎት መካከል ያለውን አለመጣጣም ለማስቀረት የሚያግዝ እንደሆነ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ኢንጂነር መላኩ እዘዘው በበኩላቸው፤ መንግሥት ባለፉት ዓመታት የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ተቋማትን በማስፋፋት በርካታ ሥራዎችን ማከናወኑን ገልፀዋል።


 

ይሁን እንጂ ከግሉ ዘርፍ ጋር ያለው ትስስር በሚፈለገው ደረጃ ባለማደጉ ገበያው በሚፈልገው ክህሎት የለማ  ብቁ የሰው ኃይል ለኢንዱስትሪው በማቅረብ በኩል ክፍተት እንዳለ አንስተዋል።

ይህንን ክፍተት ለመሙላት ኢንዱስትሪው በሚፈልገው መንገድ በማሰልጠን ከቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማት ጋር በትብብር በመሥራት የተሻለ አፈጻጸም ላሳዩ 24 ድርጅቶች እውቅና መሰጠቱን ተናግረዋል።

የንድፈ-ሃሳብና ተግባር ክህሎትን አጣምሮ የያዘ የሰው ኃይል በማፍራት ኢንዱስትሪውን ተወዳዳሪ ለማድረግ እንደሚያግዝም ፕሬዝዳንቱ ጨምረዋል። 


 

 እውቅና ከተሰጣቸው ተቋማት መካከል የቤካስ ኬሚካልስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የሰው ኃይል አስተዳደር ኃላፊ አበራ ቦሮ እና የሮሬ ሆቴል ሀዋሳ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሙሉቀን ገደፋው ከትምህርት ተቋማት ጋር አብረው መሥራታቸው ቀደም ሲል በክህሎት ይገጥም የነበረውን ክፍተት እንደቀረፈላቸው ተናግረዋል።

የከፍተኛ ትምህርት፣ ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና፣ የምርምር ተቋማትና የኢንዱስትሪ ትስስር አዋጅ ባለፈው ዓመት መጽደቁ ይታወሳል።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም