ለሀገራዊ የምክክር ሂደቱ ውጤታማነት እገዛና ትብብሩ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
ለሀገራዊ የምክክር ሂደቱ ውጤታማነት እገዛና ትብብሩ ተጠናክሮ ይቀጥላል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 7/2016(ኢዜአ)፦ለሀገራዊ የምክክር ሂደቱ ውጤታማነት እገዛና ትብብሩ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ገለጸ።
ከዚሁ መድረክ በተጓዳኝም ምክር ቤቱ ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የተሰበሰቡና ድርጅቶቹን የሚወክሉ አጀንዳዎች ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስረክቧል፡፡
የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት የምክክር ሂደቱ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ እስካሁን ሲያበረክት የቆየውን አስተዋጽኦ በማስመልከት ውይይት አድርጓል።
በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ተጠባባቂ ዋና ዳይሬክተር ሃና ወልደገብርኤል፤ ምክር ቤቱ ወሳኝ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የራሱን አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በተለይም በሰላም ግንባታ፣ በሰብዓዊ ድጋፍ እና ለሀገራዊ ምክክር ሂደት ስኬት የበኩሉን በማበርከት ላይ መሆኑን ጠቁመው ለሀገራዊ ምክክሩ መሳካት የምክር ቤቱ ድጋፍና አስተዋጽኦ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ አረጋግጠዋል።
የሲቪል ማህበራት ህብረተሰቡ ስለ ምክክር ሂደቱ ተገንዝበው በነቂስ እንዲሳተፉ ከማድረግ አንጻር የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራዎችን ጨምሮ ሌሎችንም ሲያደርጉ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡
ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የተሰበሰቡ እና ድርጅቶቹን የሚወክሉ አጀንዳዎች ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማስረከባቸውንም ተናግረዋል፡፡
ምክር ቤቱ በዛሬው ዕለት ያስረከባቸው አጀንዳዎችም የ367 የሲቪል ማህበራት መሆናቸውን ጠቁመው ይህም በአካል እና በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች የተሰበሰቡ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
በመድረኩ ሴቶችንና ወጣቶችን ወክለው የመጡ የተለያዩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ተወካዮች ዜጎች በሀገራዊ ምክክሩ ላይ እንዲሳተፉ የግንዛቤ ፈጠራ ስራዎችን መስራታቸውን ተናገረዋል፡፡
በተለያዩ አከባቢዎች የሚገኙ ሴቶች አስፈላጊነቱን ተረድተው እንዲሳተፉ ከማድረግ አንጻርም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከታቸውንም ገልጸዋል፡፡
በተለያዩ አማራጮች የግንዛቤ መፍጠር ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር አምባዬ ኦጋቶ፤ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ለምክክር ሂደቱ መሳካት እያደረጉት ላለው አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በተለያዩ ክልሎች በርካታ የማህበረሰብ ክፍሎችን በማወያየት እስካሁን ከ17 ሺህ በላይ ተወካዮችን ማስመረጥ መቻሉንም ገልጸዋል፡፡
በዚህ ሂደት ከ6 ሺህ 200 በላይ ተባባሪ አካላት መሳተፋቸውንም ጠቁመዋል፡፡
በውይይት መድረኩ የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮች፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች እና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።