በጅግጅጋ ከተማ የተከናወኑ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ለኢንቨስትመንት ፍሰት መጨመር ምቹ እድል ፈጥረዋል - ኢዜአ አማርኛ
በጅግጅጋ ከተማ የተከናወኑ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ለኢንቨስትመንት ፍሰት መጨመር ምቹ እድል ፈጥረዋል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 7/2016(ኢዜአ)፦ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በጅግጅጋ ከተማ የተከናወኑ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ለኢንቨስትመንት ፍሰት መጨመር ምቹ እድል መፍጠሩን የከተማዋ ከንቲባ ሻፊ አህመድ ገለጹ፡፡
የጅግጅጋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ፤ ሻፊ አህመድ፤ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ የጅግጅጋ ከተማ በከፍተኛ እድገት ላይ እንደምትገኝ ነው ለኢዜአ የተናገሩት፡፡
ከከተማዋ እድገት ጋር ተያይዞ የኢንቨስትመንት ፍሰቱ እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሰው፤ በተለይ በከተማዋ የተከናወኑ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ኢንቨስትመንት ለመሳብ ምቹ ሁኔታ መፍጠራቸውን ተናግረዋል፡፡
ለአብነትም አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በከተማዋ የነበረውን 10 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ወደ 35 ኪሎ ሜትር ከፍ ማድረግ መቻሉን አውስተዋል፡፡
በተጨማሪም የ31 ኪሎ ሜትር የመብራት ኃይል ማስፋፊያ ስራ መከናወኑን ጠቅሰው፤ ሌሎች ለኢንቨስትመንት የሚያስፈልጉ መሰረተ ልማቶች በስፋት እየተከናወኑ መሆኑንም እንዲሁ፡፡
በቅርቡ በ250 ሚሊዮን ብር ካፒታል በጅግጅጋ ከተማ የመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ መከፈቱን ያነሱት ከንቲባው፤ በቀጣይም የመሰረተ ልማት ስራዎችን በማሟላት ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ነው ከንቲባው ያረጋገጡት፡፡
በሌላ በኩል በሶማሌ ክልል የሰፈነው ሰላምና የጅግጅጋ ከተማ ለወደብ ያላት ስትራቴጂካዊ ቅርበት ለኢንቨስትመንት ፍሰቱ መጨመር ተጨማሪ አቅም መፍጠሩን አብራርተዋል፡