በእንሰሳት ዝርያዎች ላይ ምርምር በመስራት የዘርፉን ልማትና ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በእንሰሳት ዝርያዎች ላይ ምርምር በመስራት የዘርፉን ልማትና ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 7/2016(ኢዜአ)፦በእንሰሳት ዝርያዎች ላይ ተጨማሪ ምርምሮችን በመስራት የዘርፉን ልማትና ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ዓለም አቀፍ የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
ዓለም አቀፍ የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት (ILRI) የዘረመል ባንክ የተመሰረተበትን 40ኛ ዓመት በአዲስ አበባ አክብሯል።
በሁነቱ ላይ የተገኙት በግብርና ሚኒስቴር የእንሰሳትና ዓሳ ሃብት አማካሪ ዮሃንስ ለማ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ በእንሰሳት ሃብቷ በግንባር ቀደምትነት የምትጠቀስ ሀገር ብትሆንም በተለያዩ ምክንያቶች በአግባቡ እየተጠቀመች አለመሆኑን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም የዘርፉን ልማትና ተጠቃሚነት ለማሳደግ ቀጣይነት ያለው ምርምርና የተቀናጀ ጥረት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
በዓለም አቀፉ የእንሰሳት ምርምር ተቋም የዘረመል ባንክ ዳይሬክተር አለማየሁ ተሬሳ (ዶ/ር)፤ ኢንስቲትዩቱ የተለያዩ የእንሰሳት ዝርያዎችን በዘር ባንክ በማስቀመጥ ምርምሮችን እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የተሻሻሉ የእንሰሳት ዝርያዎችን መጠቀም፣ የተመጣጠነ የመኖ አቅርቦት፣ በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራርና ሌሎችም ቅንጅታዊ ስራዎች ለዘርፉ ልማት ወሳኝ መሆናቸውን አንስተዋል።
ለዚህም በኢንስቲትዩቱ በኩል በእንሰሳት ዝርያዎች ላይ ተጨማሪ ምርምሮችን በመስራት የዘርፉን ልማትና ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በ40 ዓመታት ውስጥ ከ20 በላይ የተሻሻሉ የእንሰሳት መኖ ዘርያዎችን በምርምር ለይቶ ለተለያዩ የምርምር ተቋማትና ለተጠቃሚዎች ማድረሱንም ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት የደንና ግጦሽ መሬት እጽዋት ብዝሃ ህይወት ምርምር መሪ ስራ አስፈጻሚ አበራ ስዩም፤ እየተመናመኑ የሚገኙ የመኖ እጽዋቶችን ለመታደግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በእንሰሳት መኖ ምርትና አቅርቦት ላይ የግሉም ዘርፍ በስፋት አንዲሳተፍና አርሶ አደሩም በእርሻው ላይ በቀላሉ የሚደርሱና ጥቅም ላይ የሚውሉ የመኖ ዝርያዎችን በስፋት ሊጠቀም ይገባል ብለዋል።