የጋምቤላ ክልል ህዝብና መንግስት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል - አቶ ኡሞድ ኡጁሉ - ኢዜአ አማርኛ
የጋምቤላ ክልል ህዝብና መንግስት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል - አቶ ኡሞድ ኡጁሉ
ጋምቤላ ፤ ግንቦት 07/2016 (ኢዜአ)፡- የጋምቤላ ክልል ህዝብና መንግስት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በተለያዩ የንቅናቄ መርሃ ግብሮች የሚያደርገውን ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ገለጹ።
''በህብረት ችለናል'' በሚል መሪ ሐሳብ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠበትን 13ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተካሂዷል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በመላው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች የጋራ ጥረት እውን የሆነ ግዙፍ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።
የጋምቤላ ክልል ህዝብና መንግስት የግድቡ ግንባታ መሠረት ከተጣለ አንስቶ ሲያደርግ የቆየውን የነቃ ተሳትፎ፤ ግንባታው እስኪጠናቀቅ ድረስ በተለያዩ የንቅናቄ መርሃ ግብሮች ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ገልጸዋል።
አክለውም በግድቡ ግንባታ ላይ የታየው ህዝባዊ አንድነት በሌሎች ልማትና በሰላም ግንባታ ስራዎች ላይም ሊደገም ይገባል ሲሉም አቶ ኡሞድ ተናግረዋል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አረጋዊ በርሔ(ዶ/ር) እንዳሉት፤ መንግስት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ለማጠናቀቅ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።
በመላው ኢትዮጵያውያን የጋራ ጥረት ተገንብቶ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ የደረሰው ታላቁ የህዳሴ ግድብ አሁን ላይ የግንባታ ሂደቱ ከ95 በመቶ በላይ መድረሱን አብራርተዋል።
የክልሉ ህዝብና መንግስት ለግድቡ ግንባታ ሲያደርግ ለነበረው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ዋና ዳይሬክተሩ አመስግነው፤ ይህን ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
በጋምቤላ ክልል የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኮማንደር ጋትቤል ቦል በበኩላቸው የጋምቤላ ህዝብ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋይ ከተቀመጠበት ጊዜ ጀምሮ ከፍተኛ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል ብለዋል።
በመሆኑም የግድቡ ግንባታ በኢትዮጵያውያን የተባበረ ክንድ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ መድረሱን ገልጸው፤ ግድቡ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለአገልግሎት እስኪበቃ ድረስ በተለያዩ መንገዶች ሲደረግ የነበረው ድጋፍ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት የሁላችን አሻራ ያረፈበት በመሆኑ ኩራት ይሰማናል" ያሉት ደግሞ በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች ናቸው።
መሆኑም የግድቡ ግንባታ ከግብ እስኪደርስ ድረስ የጀመሩትን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ቃል ገብተዋል፡፡
ዛሬ በተካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ላይ የመንግስት ሰራተኞች ፣ የንግዱ ማህበረሰብ፣ አልሚ ባለሀብቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችም ተገኝተዋል።
በዕለቱ በተደረገው የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ላይ ከቦንድ ግዢ፣ ከቲሸርትና ሌሎች ቁሳቁሶች ሽያጭ ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡ ተገልጿል።