በክህሎት ልማት የተሻለ አፈጻጸም ላሳዩ 24 ኢንዱስትሪና ድርጅቶች እውቅና ተሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
በክህሎት ልማት የተሻለ አፈጻጸም ላሳዩ 24 ኢንዱስትሪና ድርጅቶች እውቅና ተሰጠ
አዲስ አበባ ፤ ግንቦት 7/2016 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት በክህሎት ልማት የተሻለ አፈጻጸም ላሳዩ 24 ኢንዱስትሪና ድርጅቶች ለመጀመሪያ ጊዜ እውቅና ሰጠ።
እውቅና የተሰጣቸው በማሰልጠንና በመቅጠርም በኢንዱስትሪ እና ቴክኒክና ሙያ ተቋማት ትስስር የተሻለ አፈጻጸም ያሳዩ መሆናቸው ታውቋል።
የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ኢንጅነር መላኩ እዘዘው፤ እውቅናው በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማሳደግ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
የግሉ ዘርፍ በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፍ ያለውን ተሳትፎ የሚያጠናክርና ለሌሎችም አርአያ የሚሆን ነው ብለዋል።
የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ተሻለ በሬቻ፤ በምጣኔ ሃብት፣ በፈጠራና ክህሎት ብቁ የሰው ሃይል ለማፍራት የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የላቀ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል።
በዛሬው እለት ዕውቅና የተሰጣቸውም በተግባር የተደገፈ ስልጠና በመስጠትና በመቅጠር የተሻለ አፈጻጸም ያሳዩ ተቋማት መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በቀጣይም በፈጠራና ክህሎት ተወዳዳሪ የሰው ሃይል በማፍራት ረገድ የተሻለ አፈጻጸም ለሚያስመዘግቡ ተቋማትና ኢንዱስትሪዎች እውቅናው ይቀጥላል ብለዋል።
በዛሬው እለት ለተቋማቱ የተሰጠው እውቅና ከስራና ክህሎት ሚኒስቴርና ሌሎች ተቋማት ጋር በመተባበር መሆኑ ታውቋል።