ቀጥታ፡

ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የግብርና ምርቶች የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል- የዘርፉ ባለሙያዎች

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 7/2016(ኢዜአ)፦ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የኢትዮጵያ የግብርና ምርቶች የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባ የዘርፉ ባለሙያዎች ገለጹ። 

የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣን በበኩሉ የግብርና ምርቶች የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ እንዲያገኙ የህግ ረቂቅ እየተዘጋጀ ነው ብሏል።  

በኢትዮጵያ ቡና እና የቅባት እህሎችን ጨምሮ ሌሎችም የግብርና ምርቶች በብዛት ለውጭ ገበያ እንደሚቀርቡ ይታወቃል።

የተለያዩ ምርቶች ለውጭ ገበያ ቢቀርቡም ከሌሎች አገራት ጋር ሲነፃፀር የሚገኘው ገቢ አነስተኛ መሆኑ ይነገራል።

ለዚህም አንዱ ምክንያት የኢትዮጵያ የግብርና ምርቶች  የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ አለመኖር መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው በኢትዮ አልያንስ አድቮኬት የአእምሯዊ ንብረት አማካሪ የሆኑት ዶክተር ትዕግስት ደሱ እና ቃለአብ ጎሳ፤ ኢትዮጵያ በቡና ግብይት ለዘመናት የዘለቀ ልምድ ቢኖራትም ከወጪ ንግድ የምታገኘው ገቢ ግን ዝቅተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የኢትዮጵያ የግብርና ምርቶች የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር እንዳሉ ሞሲሳ፤ የግብርና ምርቶች የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ እንዲያገኙ የህግ ረቂቅ እየተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በባለስልጣኑ የማህበረሰብ እውቀትና መልክዓ ምድር አመላካች መሪ ሥራ አስፈፃሚ ታደሰ ወርቁ፤ በበኩላቸው ሀገር በቀል እውቀቶችና የመልክዓ ምድር አመላካች መብቶች ጥበቃ ላይ እየተሰራ ስለመሆኑ ተናግረዋል።


 

የማህበረሰብ እውቀቶች እንደ አዕምሯዊ ንብረትና የመልክዓ ምድር አመላካች ለማድረግም ረቂቅ ህግ እየተዘጋጀ ነው ብለዋል።

የይርጋጨፌ፣ የሐረርና ሲዳማ ቡና ምርቶች በመዳረሻ አገሮች ስሞቹ በንግድ ምልክት መመዝገባቸውን አስታውሰዋል።

 

የንግድ ምልክቶቹን የመልክዓ ምድር አመላካች ምስክር መስጠት የሚያስችል ተግባር መጀመሩንም ጠቅሰዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም