ኢትዮጵያ ከአየር ትራንስፖርት የሚመነጭ የበካይ ጋዝ ልቀትን ለመቀነስ በትኩረት እየሰራች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከአየር ትራንስፖርት የሚመነጭ የበካይ ጋዝ ልቀትን ለመቀነስ በትኩረት እየሰራች ነው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 6/2016(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ከአየር ትራንስፖርት የሚመነጭ የበካይ ጋዝ ልቀትን ለመቀነስ በትኩረት እየሰራች መሆኑን የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ገለጸ።
ባለሥልጣኑ ከአውሮፓ ኅብረት አቪዬሽን ሴፍቲ ኤጀንሲ ጋር በመተባበር ከአየር ትራንስፖርት ጋር በተያያዘ የሚመነጩ የበካይ ጋዝ ልቅትን ለመቀነስ ትኩረት ያደረገ አውደ ጥናት በአዲስ አበባ አካሂዷል።
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው መንግሥቴ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ የአቬዬሽን ኢንዱስትሪ በሕዝቦችና በአገራት መካከል ያለውን የኢኮኖሚ መስተጋብር የተሳለጠ ለማድረግ ከፍተኛ ሚና የሚጫወት ነው።
በተቃራኒውም በካይ ጋዞችን በመልቀቅ ለአየር ንብረት ለውጥ ከማጋለጥ አንጻር ድርሻ ያለው መሆኑን አስገንዝበው፤ በመከላከል ሥራ ላይ አገራት በተናጠል ከሚያከናውኑት በተጨማሪ ዓለም አቀፍ ትብብር ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከአየር ትራንስፖርት የሚመነጩ የበካይ ጋዞችን ለመቀነስ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነች መሆኗን ጠቅሰው ለአብነትም ባዮ ጋዝን ጨምሮ ታዳሽ ኃይልን ለማስፋት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
ጎን ለጎንም ኃይል ቆጣቢ አውሮፕላኖችን ወደ ሥራ የማስገባት ሥራ እንዲሁም በኤርፖርቶች አካባቢ ጋር ሊጣጣም የሚችሉ የመሰረተ ልማት ግንባታና ሌሎች በርካታ ተግባራት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በአውሮፓ ኅብረት አቪዬሽን ሴፍቲ ኤጀንሲ የፊውቸር ኢንተርናሽናል ኮርፕሬሽን የሥራ ክፍል ኃላፊ ሮድሪጎ ፕሪይጎ በበኩላቸው ኅብረቱ ከአየር ትራንስፖርት የሚመነጩ የበካይ ጋዞችን ለመቀነስ እየተሰራ ነው።
ለዚህም የተጠናከረ ዓለም አቀፍ ትስስር በመፍጠር ውጤታማ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለው አውደ ጥናት ከአየር ትራንስፖርት ጋር በተያያዘ የበካይ ጋዞች ልቀት ቅነሳ ላይ በቂ ግንዛቤ ለማስጨበጥና ትብብር ለመፍጠር ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
አውደ ጥናቱም ከዛሬ ጀምሮ እስከ ግንቦት 9/2016 ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን ከተለያዩ አገራት የተውጣጡ የአቪዬሽንና የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎችና ክፍተኛ ኃላፊዎች እየተሳተፉበት ነው።