ቀጥታ፡

ባለፉት ዘጠኝ ወራት የገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት ረገድ አበረታች ውጤት ተመዝግቧል- የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 6/2016(ኢዜአ)፦ባለፉት ዘጠኝ ወራት ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት ረገድ አበረታች ውጤት መመዝገቡን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር  መላኩ አለበል ገለጹ፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ያለፉት ዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸምን  በሚመለከት  የተለያዩ የክልል እና የከተማ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊዎች እንዲሁም የሚኒስቴሩ ተጠሪ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ውይይት ተካሄዷል፡፡


 

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በዚሁ ወቅት፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ለማሳደግ የአሰራር ማነቆዎችን በመፍታት ረገድ በተከናወኑ ስራዎች  ተስፋ ሰጪ ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል። 

ለአብነትም የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ለማሳደግ የግብዓት አቅርቦትን የማሻሻል፣ የፋይናንስና የሃይል አቅርቦትን ማሳደግ፣ እንዲሁም ከሰው ኃይል አቅርቦት አንጻር ተስፋ ሰጪ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቁመዋል። 

ይህም የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም እንዲጨምር ማስቻሉን ሚኒስትሩ ገልጸዋል። 

ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት በተሰራው ስራም 1 ነጥብ 97 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ገቢ ምርቶችን  በሀገር ውስጥ መተካት ተችሏል ነው ያሉት፡፡ 

ባለፉት ዘጠኝ ወራት በኢንዱስትሪ ዘርፉ ከ176 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል መፈጠሩንም ገልጸዋል፡፡

ከኢንዱስትሪዎች ሽግግር አኳያም ከአነስተኛ ወደ መካከለኛ የሚደረገው ሽግግር ተስፋ ሰጪ መሆኑን ገልጸው፤ ከመካከለኛ ወደ ከፍተኛ በሚደረግ ሽግግር ላይም ተጨማሪ ስራዎችን በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የስትራቴጂክ ጉዳዮች ስራ አስፈጻሚ ጥላሁን አባይ በበኩላቸው የተኪ ምርቶች ስትራቴጂ በተጨባጭ ውጤት እያስገኘ መሆኑን ገልጸዋል፡፡


 

በዚህም የጸጥታ አካላት የደንብ ልብስ፣ የቢራ ብቅልን ጨምሮ ሌሎችንም ምርቶች በሀገር ውስጥ መተካት መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ንግድ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አብዲ ሙክታር ኢንዱስትሪዎች በአካባቢው የሚመረቱ ጥሬ ዕቃዎችን እንዲጠቀሙ ከማድረግ አንጻር ውጤታማ ስራዎች በመሰራት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡   

በዚህም በአከባቢው ግብዓት ሊሆኑ የሚችሉ ምርቶችን በመለየት የማምረት ስራዎች በስፋት እየተከናወነ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡

ባለፉት ዘጠኝ ወራት በመላ ሀገሪቱ ከ83 በላይ የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖዎች የተካሄዱ ሲሆን፤ የገበያ ትስስር ከመፍጠርና ምርቶችን ከማስተዋወቅ አንጻር ትልቅ እድል መፍጠራቸውም በመድረኩ ተገልጿል፡፡ 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም