ቀጥታ፡

ባለፉት ዘጠኝ ወራት 2 ነጥብ 1 ሚሊየን ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 6/2016(ኢዜአ)፦ በአገር አቀፍ ደረጃ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 2 ነጥብ 1 ሚሊየን ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈርያት ካሚል ገለጹ።

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሀት ካሚል  ያለፉትን ዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም አስመልክቶ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በዚህም ተቋሙ የመጀመሪያውን የተቋም ግንባታ ምዕራፍ አጠናቆ ወደ ሁለተኛ ምዕራፍ መሸጋገሩን ገልጸዋል።

የዘርፉ ባለድርሻ አካላትን በማካተት "ዓመተ-ምርታማነት" የሚል ስያሜ በመስጠት እያንዳንዱ ሥራዎች ወደ ውጤት መቀየር አለበት የሚል እሳቤ ተይዞ ወደ ሥራ መገባቱን አብራርተዋል።

በክህሎት ልማት ዘርፍ ፍላጎት መር ሥርዓተ-ሥልጠና መስጠት ትልቅ ሥራ የተሰራበት መሆኑን አመላክተዋል።

ፍላጎት መር ሥርዓተ-ሥልጠና ለዘርፉ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ትልቅ ትርጉም እና ፋይዳ ያለው መሆኑን ተናግረዋል።

በቴክኒክና ሙያ ተቋማት አዳዲስ ካሪኩለም የመቅረጽ እና ጊዜውን የዋጀ የካሪኩለም ክለሳ መደረጉን አመላክተዋል።

በዚህም ባለፉት ዘጠኝ ወራት 1 ነጥብ 7 ሚሊዬን ዜጎች ፍላጎት መር ሥልጠና መውሰዳቸውን ጠቁመዋል።

የሥራ ፈጠራ በልቶ የማደር ጉዳይ ብቻ አለመሆኑን እና ይልቁንስ ኃብት መፍጠሪያ መንገድ መሆኑን አንስተዋል።

በተለያዩ ጊዜያት በተደረጉ ስምሪቶችም እሳቤውን መሬት ማውረድ መጀመራቸውን ማረጋገጥ መቻሉን አመላክተዋል።

አንዱ የሀገራዊ ሪፎርም እሳቤ ከዜጎች ተጠቃሚነት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ላይ የጠራ መረጃ ለዜጎች መስጠት መሆኑን ገልጸው፤ መንግሥት በዚህ ላይ ግልጽ አቋም ያለው መሆኑን ተናግረዋል።

የስራ ዕድል ፈጠራው ከግብርና ልማት ከኢንዱስትሪ ከኢንቨስትመት እንዲሁም ከአገልግሎት ዘርፍ ጋር ማስተሳሰር መቻሉን አስረድተዋል።

የግብርናው ዘርፍ ስራ ዕድል በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ገልጸው፤ የኢንዱስትሪ እና የአገልግሎት ዘርፍ የተሻለ የስራ ዕድል የተፈጠረባቸው እንደሆነ  ጠቅሰዋል።።

የዕቅዱ አጠቃላይ ሀገራዊ ሁኔታዎችን ከግምት በማስገባት ሰፋ ተደርጎ መታቀዱን ጠቁመዋል።

ከሥራ ዕድል ፈጠራ አንጻር ክህሎት መር እሳቤ እየተተገበረ መሆኑን ገልጸው፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 2 ነጥብ 1 ሚሊየን ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የገበያ መረጃ ሥርዓት ለአፈጻጸሙ ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።

መንግስት ለስታርትአፕ በሰጠው ልዩ ትኩረት በዘርፉ ከፍተኛ የስራ ዕድል መፍጠር እንዳስቻለ አስረድተዋል።

ስታርትአፕ በቀጣይ ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር የሚያስችል በመሆኑ በልዩ ትኩረት መስራት እንደሚገባ አመላክተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም