የቻይና ብሔራዊ የቴክስታይል እና ጨርቃጨርቅ ካውንስል በኢትዮጵያ በዘርፉ ለመሳተፍ ፍላጎት እንዳለው ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የቻይና ብሔራዊ የቴክስታይል እና ጨርቃጨርቅ ካውንስል በኢትዮጵያ በዘርፉ ለመሳተፍ ፍላጎት እንዳለው ገለጸ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 6/2016(ኢዜአ)፦ የቻይና ብሔራዊ የቴክስታይል እና ጨርቃጨርቅ ካውንስል በኢትዮጵያ የቴክስታይል እና ጨርቃ ጨርቅ ዘርፉን በጥልቀት ለመቃኘት እና ለመሳተፍ ፍላጎት እንዳለው ገልጿል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ከፍተኛ አመራሮች በዋና ጸሀፊው ዚያ ሊንግ ሚን ከተመራ የቻይናው ብሔራዊ የቴክስታይል እና ጨርቃጨርቅ ካውንስል ልዑክ ጋር ተወያይተዋል።
ካውንስሉ ዘርፉን የተመለከቱ የተለያዩ ስራዎችን የሚሰራ ሲሆን በተለያዩ ሀገራት ያሉ የጨርቃጨርቅ ልማቶች እና ያሉበትን ደረጃ በመዘዋወር ጥናት የሚያደርግ ተቋም ነው፡፡
በዚህም ካውንስሉ በኢትዮጵያ በተለይም የቴክስታይል እና ጨርቃጨርቅ ዘርፉን በጥልቀት ለመቃኘት እና ለመሳተፍ ፋላጎት እንዳለው ገልጿል።
በኮሚሽኑ እና በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አመራሮችም በዘርፉ ያሉ ዕድል እና አማራጮች፣ ማበረታቻዎች እንዲሁም የፖሊሲ ማሻሻያዎች ዙሪያ ለልዑኩ ሰፊ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡
ከልዑኩ ጋር የአንድ ለአንድ ውይይት የተደረገ ሲሆን በውይይቱ ለተነሱ ሃሳቦች እና ጥያቄዎችም ግብረ መልስ መሰጠቱን ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል።