ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የኮሙኒኬሽን ሳተላይት ባለቤት ለመሆን እየሰራች ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 6/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የኮሙኒኬሽን ሳተላይት ባለቤት ለመሆን እየሰራች መሆኑን የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

የኢትዮ-ሳት ካምፓኒ ከደንበኞቹና አጋር አካላት ጋር በኢንዱስትሪው እድገት ላይ ትኩረት ያደረገ አውደ ጥናት አካሂዷል።


 

በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ምክትል ዳሬክተር ቤተልሄም ንጉሴ፤ የኢትዮ-ሳት አገልግሎት ኢትዮጵያ ለሳተላይት የምታወጣውን ከፍተኛ ወጪ መቀነሱን ገልጸዋል።

ኢትዮ-ሳት ባህልን ከማስጠበቅ አንጻርም እያበረከተ ያለውን የላቀ አስተዋጽኦ አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በቀጣይ የኮሙኒኬሽን ሳተላይት ባለቤት ለመሆን እየሰራች ስለመሆኑም ምክትል ዳይሬክተሯ ተናግረዋል። 

ኢትዮጵያ በታህሳስ 10 ቀን 2012 ዓ.ም በታሪኳ የመጀመሪያዋን ETRSS-01 የመሬት ምልከታ ሳተላይት ወደ ህዋ የላከች ሲሆን በታህሳስ 2013 ዓ.ም ደግሞ ET-Smart-RSS የተባለችውን ሁለተኛዋን የመሬት ምልከታ ሳተላይት ማምጠቋ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መሀመድ ኢድሪስ፤ በኢትዮሳት አሁን ላይ ከ70 በላይ የኃይማኖት፣ የንግድ፣ የህዝብና ሌሎች የሀገር ውስጥ ቻናሎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።



 

የኢትዮ ሳት አገልግሎትም 17 ሚሊዮን ቤቶች ላይ መድረሱን ገልጸው ይህም ከተደራሽነት አንጻር ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም እስካሁን የተገኙ ውጤቶችን በማስቀጠል በቀጣይ ትኩረት መደረግ ያለባቸውን ጉዳዮች ለይቶ መስራት ይገባል ብለዋል።

የዓለም አቀፉ የሳተላይት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት አቅራቢ (SES) የኢትዮጵያ ዳይሬክተርና የምስራቅ አፍሪካ የሽያጭ ሃላፊ መነን አገኘሁ፤ በኢትዮጵያ ከ18 ነጥብ 2 ሚሊዮን ቲቪ ተጠቃሚዎች መካከል 17 ሚሊዮኑ በኢትዮ-ሳት ስርጭት እያገኙ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2017 ከነበረው ቴሌቪዥን ተጠቃሚ አንጻር አሁን ላይ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው የኢት-ሳት ተደራሽነትም እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል። 

በሀገሪቱ ከሚገኙ 136 የሬዲዮና የቴሌቪዥን ቻናሎች መካከል 70 የሚሆኑት የሀገር ውስጥ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

ኢትዮ-ሳት በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ማህበር፣ በቀድሞ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን፣ በቀድሞው ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት እና SES በጋራ በ2012 ዓ.ም እውን መደረጉ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም