የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ከተፈጥሮ ኃብት ጥበቃ ባለፈ ዘርፈ-ብዙ ጥቅሞችን የሰነቀ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ከተፈጥሮ ኃብት ጥበቃ ባለፈ ዘርፈ-ብዙ ጥቅሞችን የሰነቀ ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 6/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ ልማት ከተፈጥሮ ኃብት ጥበቃ ባለፈ ዘርፈ-ብዙ ጥቅሞችን የሰነቀ መሆኑን የመርሃ-ግብሩ ብሔራዊ የቴክኒክ ኮሚቴ አስተባባሪ አደፍርስ ወርቁ(ዶ/ር) ገለጹ።
ለዘንድሮው የ2016/17 በጀት ዓመት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብርም ከ6 ነጥብ 5 ቢሊየን በላይ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የብሔራዊ አረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የቴክኒክ ኮሚቴ አስተባባሪ አደፍርስ ወርቁ(ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የተፈጥሮ ኃብትን ከመጠበቅ ባለፈ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረግ ጥረት አካል መሆኑን ገልጸዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ከተጀመረ በኋላ የደን ውድመትን በመከላከል የተፈጥሮ ኃብትን መጠበቅና የደን ሽፋን እንዲጨምር ያስቻለ ስለመሆኑም አንስተዋል።
በዚህም መርሃ ግብሩ በረሃማነትን መከላከል፣ የድርቅ አደጋን መቀነስና የመሬት መራቆትን መታደግን ጨምሮ ዘርፈ-ብዙ ዓላማን የሰነቀ መሆኑንም ተናግረዋል።
በችግኝ ጣቢያና በጥብቅ ሥፍራዎች በእንስሳት ማድለብ፣ በንብ ማነብ፣ በዶሮ እርባታ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ የሥራ ዕድል በመፍጠር ብዙዎችን ተጠቃሚ እያደረገ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃም የኢትዮጵያን ገጽታ በመገንባት ረገድ የላቀ አስተዋጽዖ እያበረከተ መሆኑን ገልፀዋል።
በአረንጓዴ አሻራ ለተገኘው እውቅና እና ለተመዘገበው ስኬት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፤ ሚና ከፍተኛ መሆኑን አስታውሰዋል።
ኢትዮጵያ ባስመዘገበችው ስኬት መነሻነት ጎረቤት ሀገራትን ጨምሮ ሌሎች ሀገራትን ማነሳሳቱን ገልፀዋል።
ለዘንድሮው የ2016/17 በጀት ዓመት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ከ6 ነጥብ 5 ቢሊየን በላይ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅቱ ተጠናቋል ብለዋል።
በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ለመትከል የአፈርና ውሃ ጥበቃ ከተሰራበት 1 ነጥብ 8 ሚሊየን ሄክታር መሬት ውስጥ 504 ሺህ ሄክታሩን የካርታ መገኛ ልኬት እንደተዘጋጀ አስረድተዋል።
የካርታ መገኛ ልኬቱም ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቀነስ የምትጫወተውን ገንቢ ሚና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የችግኝ ዝግጅትና የተከላ መርሃ-ግብሩን በቀላሉ እንዲገነዘብ ያስችላል ብለዋል።
የ2016/17 በጀት ዓመት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብርን ለማስጀመር ሳምንታዊና ወርሃዊ ዕቅድ ተዘጋጅቶ እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል።
በርካታ ዜጎች የሚሳተፉበትን የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር በዓለም የድንቅ ሥራ መዝገብ "ጊነስ ቡክ ኦፍ ወርልድ ሪከርድስ" ለማስመዝገብ ጥያቄ መቅረቡንም አስታውቀዋል።
ለዝግጅቱም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አነሳሽነት ባለፉት ዓመታት የተወሰዱ ልምዶችን በመቀመር በዜጎች ተሳትፎ ስኬታማ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።
በአጠቃላይ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የአየር ንብረት ተጽዕኖን በመቀነስ ለኢትዮጵያ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊ፣ ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ መስኮች ዘርፈ-ብዙ ፋይዳ እያስገኘ እንደሚገኝም አደፍርስ ወርቁ(ዶ/ር) አስገንዝበዋል።