ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የቅርስ ምርምር ጉባዔና አውደ ርዕይ ተጀመረ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 6/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የቅርስ ምርምር ጉባዔና አውደ ርዕይ "የኢትዮጵያ ቅርስ ትላንት፣ ዛሬና ነገ" በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በመርሃ ግብሩ ላይ ሚኒስትሮችና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ በርካታ ምሁራንና የተቋማት አመራሮች ተገኝተዋል።


 

የቱሪዝም ሚኒስትሯ አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ፤ የበርካታ እምቅ የቱሪዝም ሃብቶች ባለቤት የሆነቸው ኢትዮጵያ ሃብቷን በማልማት ዋነኛ የእድገት አማራጭ ለማድረግ እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል። 

በመሆኑም የሀገር መለያና ሃብት የሆኑትን ቅርሶች በአግባቡ ጠብቆ ለትውልድ ማስተላለፍ ተገቢ መሆኑን አንስተዋል።

በዚህ ረገድ መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሯ የህብረተሰቡም እገዛና ትብብር ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ከተቋቋመ ከ1936 ዓ.ም ጀምሮ በ80 ዓመት ጉዞው 11 የማይዳሰሱና 5 የሚዳሰሱ ቅርሶችን በተባበሩት መንግስታት የትምህርትና ሳይንስ የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ማስመዝገቡንም ሚኒስትሯ አስታውሰዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያን በቅርስ ምርምር የልህቀት ማዕከል በማድረግ ከሀገር አልፎ በአፍሪካና በዓለም ተጠቃሽ ማድረግ የሚቻል መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን  ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው፤ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ቅርሶች የትናንት ታሪካችን፣  የዛሬ የማንነታችን መገለጫዎችና የሀገር ሃብቶች በመሆናቸው ልንጠብቃቸው ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ የቅርስ ምርምር ጉባዔና አውደ ርዕይ ዛሬ እና ነገ የሚካሄድ መሆኑ ታውቋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም