ቀጥታ፡

የኢትዮ ሳት አገልግሎትና ተደራሽነት ከፍተኛ እድገት እያሳየ ነው - የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 6/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮ ሳት አገልግሎትና ተደራሽነት ከፍተኛ እድገት እያሳየ መሆኑን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ገለጸ።

የኢትዮ ሳት ካምፓኒ ከደንበኞቹና አጋር አካላት ጋር በኢንዱስትሪው እድገት ዙሪያ ትኩረት ያደረገ አውደ ጥናት በአዲስ አበባ እያካሄደ ነው።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መሀመድ ኢድሪስ፤ በኢትዮ ሳት አሁን ላይ ከ70 በላይ የኃይማኖት፣ የንግድ፣ የህዝብና ሌሎች የሀገር ውስጥ የቴሌቪዥን ቻናሎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

የኢትዮ ሳት ተደራሽነት ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው እስከ አሁን የመጣበትን ሂደት በመገምገም በቀጣይ ትኩረት መደረግ ያለባቸው ጉዳዮችን መለየት ይገባል ብለዋል።

ለዚህ ጥረትም ባለስልጣኑ ድጋፍና ትብብር እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር ቤተልሄም ንጉሴ፤ ኢትዮጵያ ለሳተላይት የምታወጣውን ከፍተኛ ወጪ ከመቀነስና ባህልን ከማስጠበቅ አንጻር እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ አንስተዋል።

ኢትዮጵያ የራሷ የኮሙኒኬሽን ሳተላይት እንዲኖራት እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ኢትዮ ሳት በ2012 ዓ.ም በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ማህበር፣ በቀድሞ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣንና በቀድሞው ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በጋራ እውን የሆነና አሁን ላይ 136 ቻናሎች በውስጡ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም