ምክር ቤቱ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ረቂቅ አዋጅን አፀደቀ - ኢዜአ አማርኛ
ምክር ቤቱ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ረቂቅ አዋጅን አፀደቀ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 6/2016(ኢዜአ)፦ ምክር ቤቱ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ረቂቅ አዋጅን አፀደቀ።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ26ኛ መደበኛ ስብሰባው የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ረቂቅ አዋጅን በሙሉ ድምፅ አፅድቋል።
የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች ረቂቅ አዋጁን አስመልክቶ ለምክር ቤቱ ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ አቅርበዋል።
ረቂቅ አዋጁ ከጊዜው ጋር አብሮ የሚሄድ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ስርዓት ለመዘርጋት የሚያስችል መሆኑም ነው የተገለጸው።
ረቂቅ አዋጁ አርሶና አርብቶ አደሩ ከደረሰበት ሁለንተናዊ ዕድገት ጋር ኑሮውን እንዲያሻሽልና በንብረቱ መጠቀም እንዲችል የሚያደርግ ነው ተብሏል።
የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሰለሞን ላሌ እንዳሉት ረቂቅ አዋጁ ሴቶችን ጨምሮ ልዩ ድጋፍ የሚሹ ሰዎችን የመሬት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ነው ብለዋል።
አርሶ አደሩ ንብረቱን አስይዞ የፋይናንስ ድጋፍ እንዲያገኝና ምርትና ምርታማነቱን እንዲያሳድግ የሚያግዝ እንደሆነም ነው ያብራሩት።
ምክር ቤቱና የሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች በረቂቅ አዋጁ ላይ ሰፊ ጊዜ ሰጥተው ውይይት ማድረጋቸውንና የሚመለከታቸውን አካላት ማወያየታቸውንም አመልክተዋል።
ምክር ቤቱ ረቂቅ አዋጁ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ በሙሉ ድምፅ አፅድቋል።
በሌላ በኩል ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ የሜዳይ፣ ኒሻንና ሽልማት ረቂቅ አዋጅን አጽድቋል።
ረቂቅ አዋጁ እስካሁን ድረስ በተበታተነ መልኩ ዝርዝር ማስፈጸሚያ ደንብ ሳይኖረው ሲሰጥ የነበረው የሜዳይ፣ ኒሻንና ሽልማት ሥነ-ሥርዓት ሕጋዊ ሥርዓት ለማበጀት የሚያስችል መሆኑም ተገልጿል።
በምክር ቤቱ የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች እንዲሁም የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች ረቂቅ አዋጁ በአገር፣ አህጉርና፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ሥራ የሰሩ ግለሰቦች ተገቢው ዕውቅናና ክብር እንዲያገኙ የሚያደርግ መሆኑን አብራርተዋል።
ምክር ቤቱ የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ የሁለት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች የሥራ ስንብትን አስመልክቶ ያቀረበውን የውሳኔ ሀሳብም ለዝርዝር ዕይታ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።
የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ማሻሻያ፣ የኢትዮጵያ ደረጃዎች ረቂቅ አዋጅ፣ የሕጋዊ ስነ-ልክ ረቂቅ አዋጅ እንዲሁም ተጨማሪ እሴት ታክስ ረቂቅ አዋጅም ለዝርዝር ዕይታ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች ተመርቷል።