በሲዳማ ክልል በ2016/2017 መኸር እርሻ አሲዳማ አፈርን በማከም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በሲዳማ ክልል በ2016/2017 መኸር እርሻ አሲዳማ አፈርን በማከም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል
ሀዋሳ፣ ግንቦት 6/ 2016 (ኢዜአ) :- በሲዳማ ክልል በ2016/2017 ምርት ዘመን አሲዳማ አፈርን በማከም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።
"የአፈር ጤናማነት ለሀገር ህልውና" በሚል መሪ ሐሳብ ቢሮው ለልማት ሠራተኞች፣ ለዘርፉ አመራር አባላትና ባለሙያዎች የሁለት ቀናት ስልጠና በዳዬ፣ አለታ ወንዶ፣ ይርጋ ዓለምና ሀዋሳ ማዕከላት እየሰጠ ነው።
በሀዋሳ ስልጠና ማዕከል ላይ የተገኙት የሲዳማ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ መምሩ ሞኬ እንዳስታወቁት በክልሉ አሲዳማ አፈር የግብርና ምርትና ምርታማነት ላይ እያስከተለ ያለውን ችግር ለመፍታት በአፈር ማከም ላይ ትኩረት ተደርጓል።
ለስራው የተሰጠው ትኩረት ከችግሩ ጋር ሲነፃጸር አሁንም ብዙ ስራ መስራት እንደሚጠይቅ የተናገሩት የቢሮው ኃላፊ፤ የአፈር ጤንነትን ለመጠበቅ ስራውን በአግባቡ ከሰራን ምርትና ምርታማነት ላይ ለውጥ ማምጣት ይቻላል ብለዋል።
የስልጠና መድረኩም በተለይም የኖራ አቅርቦትና ስርጭት እንደ ሌሎች የግብርና ግብዓቶች አቅርቦት ስርዓት ውስጥ አካቶ ማቅረብ የሚያስችል ሁኔታን ለማመቻቸት ያለመ ነው ብለዋል።
በመሆኑም 2016/2017 ምርት ዘመን በመኸር እርሻው ቀዳሚ ተግባራት መካከል አሲዳማ አፈር ያለባቸው አካባቢዎችን ለማከም የሚያስችሉ ተግባራትን ማከናወን ነው ብለዋል።
የቢሮው የተፈጥሮ ሀብትና መሬት አስተዳደር ዘርፍ ኃላፊ አቶ ፍቅረእየሱስ አሸናፊ በበኩላቸው በ2016/2017 ምርት ዘመን በመኸር እርሻ ከሚለማው 98 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ውስጥ 2 ሺህ 544 ሄክታር የሚሆነው አሲዳማ አፈር ያለበት መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህንን መሬት ለማከምም በ22 ወረዳዎች እና በ115 ቀበሌዎች ለተመረጡ ልማት ሠራተኞች እና ለዘርፉ አመራሮች በአራት ክላስተር ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን አስረድተዋል።
በምርት ዘመኑ በአሲዳማነት የተጠቃውን መሬት ለማከም ከ70 ሺህ ኩንታል በላይ ኖራ እንደሚቀርብ አስታውቀዋል።
ለአንድ ሄክታር 30 ኩንታል ኖራ አንዴ በመጠቀም ከዚያ ቀጥሎ ባሉት አምስት ተከታታይ ዓመታት አርሶ አደሩ ሌላ ኖራ ሳይጠቀም ምርትና ምርታማነት ማሳደግ እንደሚችል አስረድተዋል።
የስልጠናው ተሳታፊዎችም የተሰጣቸውን ግንዛቤ በመጠቀም አርሶ አደሩ መሬቱን በአግባቡ በመያዝ ምርትና ምርታማነት ማሳደግ ላይ እንዲያተኩር የማድረግ ሃላፊነት እንዳለባቸው ነው ያነሱት።
በዚህም በክልሉ ምርትና ምርታማነትን ለማሰደግ አሲዳማ አፈር ለማከም በሚደረገው ሂደት ውስጥ የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባም አስረድተዋል።