በኢትዮጵያ አምራች ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ የሀገር ውስጥ ምርቶችን የመጠቀም ባህልን ማዳበር ይገባል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ አምራች ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ የሀገር ውስጥ ምርቶችን የመጠቀም ባህልን ማዳበር ይገባል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 6/2016(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን አቅም በማጎልበት ጸጋዎችን ማልማት እና የሀገር ውስጥ ምርቶችን የመጠቀም ባህልን ማዳበር እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ከግንቦት 1 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ለአምስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ታምርት የ2016 ኤክስፖ ማጠቃለያ መርሐ ግብር ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎችና የአምራች ኢንዱስትሪ ተወካዮች በተገኙበት ተካሂዷል።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ሰፊ የስራ ዕድል በመፍጠር ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት፣ ጥራት ያለው ምርት ለውጭ ገበያ በማቅረብ የሀገሪቱን ጥቅል ኢኮኖሚያዊ እድገት ድርሻ ለማሳደግ ያለመ ነው።
በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ንቅናቄውን በይፋ ካስጀመሩበት ከሚያዚያ/2014 ዓ.ም ጀምሮ ተዘግተው የነበሩ በርካታ አምራች ኢንዱስትዎች ወደ ስራ ገብተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በኢትዮጵያ ታምርት የ2016 ኤክስፖ ማጠቃለያ መርሐ ግብር ላይ እንዳሉት፤ ንቅናቄው ተኪ ምርቶችን ከማቅረብም ባለፈ ለውጭ ገበያ በማዘጋጀት በአምራች ዘርፉ ላይ መነቃቃት እንዲፈጠር አድርጓል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪውን ምርታማነትና ተወዳዳሪነት ውስን እንዲሆን አድርገው የቆዩ ችግሮችን በመለየት ደረጃ በደረጃ እየተፈቱ መሆኑን ተናግረዋል።
በንቅናቄው አምራች ኢንዱስትሪው ከየት ተነስቶ የት መድረስ እንዳለበት ትልም ከማስቀመጥም ባለፈ ተኪ ምርቶችን በማምረት ተጨባጭ ለውጥ ተመዝግቧል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ታምርት ዓላማ ዘርፉ በሚፈለገው ልክ እንዳያድግ ያደረጉ ችግሮችን መለየት እና የልማት እድሎችን መጠቀም መሆኑንም ገልጸዋል።
በዚህም መንግስት ለጀመረው የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር መሰረት የሚሆኑ ውጤቶች በአምራች ዘርፉ እየተመዘገቡ መሆኑን ገልጸው፥ የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ዓላማውን ከግብ በማድረስ የተሳካ እንደነበር ጠቅሰዋል።
በቀጣይም በአምራች ኢንዱስትሪዎች ዘንድ ያሉ ማነቆዎችን በመፍታት ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ ጸጋ በአግባቡ ለመጠቀም የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የመንግስት ተቋማት የሀገር ውስጥ አምራቾችን ምርት እንዲጠቀሙ የማድረግ ስትራቴጂ ተግባራዊ ይደረጋል ነው ያሉት።
ለአምራቾች ዘላቂ የገበያ ትስስር መፍጠርና በሀገር ወስጥ ምርት የመኩራት እሴትን በዘላቂነት መገንባት የሁሉም ቀጣይ የቤት ስራ እንደሆነ አስገንዝበዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፤ ኤክስፖው የአምራች ኢንዱስትሪውን ማነቆዎች ለመፍታት የፖሊሲ አውጭዎችና አምራቾች እንዲገናኙ ያስቻለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዚህም ተኪ እና ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን በስፋትና በጥራት በማምረት ስኬቶች የተመዘገቡበት ነበርም ብለዋል።
በኤክስፖው ከመቶ ሺህ በላይ ግለሰቦችና ተቋማት መሳተፋቸውን ገልጸው፣ ከ57 ሀገሮች የመጡ ድርጅቶች እንዲሁም 157 ዲፕሎማቶች መገኘታቸውን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ አምራች ኢንዱስትሪዎች ምርት ከሀገር ውስጥ ፍጆታ ባለፈ እንደ ጣሊያን፣ ሩሲያ፣ ኬንያና ሌሎች የአውሮፓና አፍሪካ ሀገሮች ተፈላጊነቱ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡
አጠቃላይ 130 ከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ጨምሮ 210 አምራቾች መሳተፋቸውን ገልጸው፤ በዚህም 5 ሺህ 188 የግብይት ትስስር በመፍጠር ከሶስት ቢሊዮን ብር በላይ ግብይት ተከናውኗል ብለዋል፡፡
ሚኒስትሩ አክለውም ኤክስፖው ኢትዮጵያ ያለቀለት ምርት ብቻ ሳይሆን ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ማሽነሪዎችን ማምረት የሚችሉ ልጆች እንዳሏትም ያሳየ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የ2017 ኤክስፖ ከሚያዚያ 30 እስከ ግንቦት 6 ቀን 2017 ዓ.ም ለሰባት ቀን እንዲካሄድ መወሰኑንም ጠቁመዋል።