ለአምራች ኢንዱስትሪዎች እየተደረገ ያለው ድጋፍ የማምረት አቅማቸው እንዲጨምር አድርጓል - የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ለአምራች ኢንዱስትሪዎች እየተደረገ ያለው ድጋፍ የማምረት አቅማቸው እንዲጨምር አድርጓል - የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 6/2016(ኢዜአ)፦ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች እየተደረገ ያለው ልዩ ድጋፍና ማነቆዎችን የመፍታት ስራ የማምረት አቅማቸው እንዲጨምር አድርጓል ሲሉ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለጹ።
የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተያዘው በጀት ዓመትን ያለፉት ዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ በአዲስ አበባ እያካሄደ ነው።
በመድረኩ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፤ የተቋሙ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የተለያዩ የክልል እና የከተማ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊዎች እንዲሁም የተጠሪ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
አቶ መላኩ አለበል ባለፉት ዘጠኝ ወራት በኢንዱስትሪ ዘርፉ ትልልቅ ተግባራት ታቅደው መከናወናቸውን ገልጸዋል።
የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ለማሳደግ በተሰሩ ስራዎች የነበሩ ማነቆዎችን ከመፍታት ጀምሮ አስፈላጊ የሚባሉ ድጋፎች በመደረጋቸው ተስፋ ሰጪ ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።
ለአብነትም የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ለማሳደግ የግብዓት አቅርቦትን የማሻሻል፣ የፋይናንስና የሃይል አቅርቦትን ማሳደግ፣ እንዲሁም ከሰው ሃይል አቅርቦት አንጻር ተስፋ ሰጪ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቁመዋል።
ይህም የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም እንዲጨምር ማስቻሉን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ በተሰራው ስራም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ44 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን አስረድተዋል።
ከኢንዱስትሪዎች ሽግግር አኳያም ከአነስተኛ ወደ መካከለኛ የሚደረገው ሽግግር ተስፋ ሰጪ መሆኑን ገልጸው፤ ከመካከለኛ ወደ ከፍተኛ በሚደረግ ሽግግር ላይም ተጨማሪ ስራዎችን መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት በመላ ሀገሪቱ ከ83 በላይ የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖዎች መካሄዳቸውን ጠቁመው፤ ይህም የገበያ ትስስር ከመፍጠርና ምርቶችን ከማስተዋወቅ አንጻር ትልቅ እመርታ ያሳየ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በትናንትናው ዕለት የተጠናቀቀው የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖው በውጤታማነት እንዲጠናቀቅ ላደረጉ አካላትም አቶ መላኩ ምስጋና አቅርበዋል።