ቀጥታ፡

የኢትዮ-ብራዚል የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም በሳኦ-ፖሎ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 6/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮ-ብራዚል የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም በብራዚል ሳኦ-ፖሎ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

ፎረሙን ዋፋ ማርኬቲንግና ፕሮሞሽን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ ከብራዚል ኤምባሲ እና በብራዚል ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር በመተባበር ነው ያዘጋጀው፡፡

በፎረሙ በብራዚል የኢትዮጵያ አምባሳደር ጣፋ ቱሉ፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴዔታ ፍስሐ ይታገሱ ፣ የብራዚል የንግድ የኢንዱስትሪና አገልግሎት ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ሃላፊ ማርሲዮ ኤልያስ ሮዛ እና ሌሎች የሥራ ሃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡


 

ከዚህ ባፈም ከ250 በላይ ከኢትዮጵያ እና ብራዚል የተወጣጡ ባለሐብቶች እና ኩባንያዎች መሳተፋቸው ተገልጿል።

ፎረሙ ኢትዮጵያን የብራዚል ባለሃብቶችና ኩባንያዎች ዋነኛ የኢንቨስትመንት መዳረሻ በማድረግ ረገድ ትልቅ አበርክቶ እንደሚኖረው ተጠቅሷል፡፡

በተለይም በግብርና እና አግሮፕሮሰሲንግ፣ በኢንዱስትሪ፣ በማዕድን፣ በጨርቃጨርቅና በሌሎች የኢንቨስትመንት ዘርፎች ያለውን ሰፊ ዕድል መጠቀም ያስችላል ተብሏል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያውያን ባለሃብቶች ከብራዚል አቻዎቻቸው ጋር ትስስር ለመፍጠር እንዲሁም የሀገራቸውን ምርቶች በብራዚል ገበያ በስፋት ተደራሽ ማድረግ እንደሚያስችል ተጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም