የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ማነቆዎች በመፍታት ስኬቶች የተመዘገቡበት ነው-ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ማነቆዎች በመፍታት ስኬቶች የተመዘገቡበት ነው-ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 5/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚያጋጥሟቸውን ማነቆዎች በመፍታትና የመልማት እድሎችን በመጠቀም ስኬቶች የተመዘገቡበት መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት የኢትዮጵያ ታምርት የ2016 ኤክስፖ ማጠቃለያ መርሐ ግብር ላይ ነው።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪውን ምርታማነትና ተወዳዳሪነት ውስን እንዲሆን አድርገው የቆዩ ችግሮችን በመለየት ደረጃ በደረጃ እየተፈቱ መሆኑን ተናግረዋል።
በንቅናቄው አምራች ኢንዱስትሪው ከየት ተነስቶ የት መድረስ እንዳለበት ትልም ከማስቀመጥም ባለፈ ተኪ ምርቶችን በማምረት ተጨባጭ ለውጥ ተመዝግቧል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ታምርት ዓላማ ዘርፉ በሚፈለገው ልክ እንዳያድግ ያደረጉ ችግሮችን መለየት እና የልማት እድሎችን መጠቀም መሆኑንም ገልጸዋል።
በዚህም መንግስት ለጀመረው የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር መሰረት የሚሆኑ ውጤቶች በአምራች ዘርፉ እየተመዘገቡ መሆኑን ገልጸው፥ የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ዓላማውን ከግብ በማድረስ የተሳካ እንደነበር ጠቅሰዋል።
በቀጣይም በአምራች ኢንዱስትሪዎች ዘንድ ያሉ ማነቆዎችን በመፍታት ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ ጸጋ በአግባቡ ለመጠቀም የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የመንግስት ተቋማት የሀገር ውስጥ አምራቾችን ምርት እንዲጠቀሙ የማድረግ ስትራቴጂ ተግባራዊ ይደረጋል ነው ያሉት።
ለአምራቾች ዘላቂ የገበያ ትስስር መፍጠርና በሀገር ወስጥ ምርት የመኩራት እሴትን በዘላቂነት መገንባት የሁሉም ቀጣይ የቤት ስራ እንደሆነ አስገንዝበዋል።