ቀጥታ፡

መንግስት ለኢትዮጵያ አቪዬሽን ዘርፍ እድገት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እያደረገ ነው - ዶክተር ዓለሙ ስሜ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 5/2016(ኢዜአ)፦ መንግስት ለኢትዮጵያ አቪዬሽን ዘርፍ እድገት ቀጣይነት ያለው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ገለጹ።

12ኛው የአፍሪካ አቪዬሽን የባለድርሻ አካላት ጉባኤ "የአፍሪካን አቪዬሽን ከማስተሳሰር ባሻገር" በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።

ጉባኤው ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ቀናት የሚቆይ ሲሆን የዘርፉ ተወካዮች መጪው ጊዜ ለአህጉሪቱ የአቪዬሽን መስክ ይዞ በሚመጣው እድል፣ በአፍሪካ አየር ትራንስፖርት ደህንነት፣ ኦፕሬሽን እና መሰል ጉዳዮች ላይ ይመክራል ተብሏል።

የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትሩ ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) በጉባኤው መክፈቻ ወቅት እንዳሉት፤ የአየር ትራንስፖርት ዘርፍ ዓለም አቀፍ ኢኮኖሚን ለማንቀሳቀስ ቁልፍ ሚና አለው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድም በሀገሪቱ ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገትን በማረጋገጥ ረገድ የማይተካ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

በመሆኑም የአየር መንገዱን እድገትና የአቪዬሽን መስኩን የሽግግር ልህቀት ለማረገጋገጥ መንግስት ሁሉን አቀፍ እና ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እያደረገ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው፣ አየር መንገዱ አፍሪካን እና የተቀረውን ዓለም በአየር ትራንስፖርት የማስተሳሰር ዕቅዱን እያሳካ ነው ብለዋል።


 

የአፍሪካን የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር አየር መንገዶቹ ተቀራርበው መስራት እንደሚገባቸው  ገልጸው፥ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቀዳሚነት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

መጪው ጊዜ የአየር ትራንስፖርት በአህጉሪቱ በይበልጥ የሚፈለግበት በመሆኑ ከወዲሁ በሰው ሃይልና  ዘርፉ በሚጠይቀው  ሁሉ መዘጋጀት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከደረሰበት ስኬት አኳያ ለአፍሪካ አየር ትራንስፖርት እድገት ድጋፍ እንደሚያደርግም ነው የተናገሩት።

የአፍሪካ አየር መንገዶች ማህበር /አፍራ/ ዋና ፀሐፊ አብዱራህማን በርቴ፣ ጉባኤው የአፍሪካን የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ተግዳሮትና ያሉ እድሎችን ለመመልከት የሚያስችል ነው ብለዋል።


 

የአህጉሪቱን አቪዬሽን ኢንዱስትሪ ማስተሳሰርና በጋራ ማሳደግም ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታው የላቀ መሆኑን ጠቁመዋል።

በጉባኤው ሚኒስትሮች፣ የአፍሪካ አየር መንገዶች ሃላፊዎች፣ የዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፓርት ማህበር /አያታ/ የአውሮፕላን አምራቾችና የዘርፉ ባለሙያዎች ታድመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም