በአንድነት የመምከር ብሩህ ተስፋ! 

በአንድነት የመምከር ብሩህ ተስፋ! 

በቀደሰ ተክሌ (ከሚዛን አማን)

ሀሳብ ያፋቅራል፤ ሀሳብ ያቃርናል። በማንኛውም ጊዜ የሚነሳ ሀሳብ በውይይት ዳብሮ በሰዎች የሕይወት ኡደት ውስጥ መግባባት፣ መተማመን እና መስማማት የሚሉ መሠረታውያንን ሲያስከትል ሰዎችን ልብ ለልብ በማገናኘት አንድ የማድረግ ኃይሉ ከፍያለ ይሆናል። ያን ጊዜ ሰላምና ፍቅር በአብሮነት ታጅቦ በጋራ ማንነት ይደምቃል። 

በተቃራኒው ሀሳብ በልዩነት የተወጠረ ከሆነ በጊዜ ሂደት እየከረረ ወዳጅነትን የመበጠስ አቅም ያገኛል። ይህ እንዳይሆን ሀሳቦችን በውይይት ማቀራረብ የመጀመሪያ ጉዳይ የመጨረሻም መፍትሄ ነው።  ሰው እንደመልኩ አስተሳሰቡና ግንዛቤው ቢለያይም ዙሮ አንድ የሚሆንበት ሰብዓዊ ፀጋ ተችሮታል። ይህም ከራስ በተጨማሪ የሌሎችንም ሀሳብ አዳምጦ የጋራ መግባባት ላይ መድረስ የሚያስችል ማስተዋል ነው። ማስተዋል ደግሞ ግራ ቀኝን የመቃኘትና የመመዘን ጥበብ ሲሆን፤ የሌሎችን ሀሳብ ከእውነታ ጋር ለማጤን ይረዳል።

መነጋገር በብዝኃ አስተሳሰብ እና ማንነት ውስጥ የመከባበር እሴትን በማጉላት በሕዝቦች መካከል አንድነትንና መቀራረብን ይፈጥራል። ፍቅር ሰብኮ፣ ሰላም ዘርቶ አብሮነትን ለማጨድ የሚያስችል ከጥንትም በማህበረሰቡ ወስጥ ያለው ጥበብ ውይይት ነው።

ማህፀነ ለምለሟ ኢትዮጵያ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችን ከብዝሃ ባህልና እምነት ጋር አቅፋ ይዛለች። ብዝኃነት ውስጥ ያለው ኢትዮጵያዊነት ስሟን በአብሮነት የመኖር ተምሳሌት የሚያስጠራ ነው። 

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ በሚያዘጋጀው ምቹ ሁኔታ ኢትዮጵያዊያን በችግሮቻቸው ላይ በጋራ ሊመክሩ ነው። በምክክሩም "የኢትዮጵያዊነት ቀለም፣ የአብሮነት መንፈስ፣ የመከባበር እና የሰላም እሴት አብቦ ፍሬው በምድሪቱ እንዲታይ ያደርጋል" የሚል ብሩህ ተስፋን ሰንቀዋል። ለችግሮቻቸው መፍቻ ቁልፍ ውይይት መሆኑን ስለተረዱትም ምክክሩን አጥብቀው ሽተዋል። 

በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ደህንነት መምህር እንዳለ ንጉሴ እንደሚሉት፤ በአብዛኛው የአፍሪካ ሀገራት ችግሮች ሲፈጠሩ ለመፍትሄው አፈ ሙዝ እንጂ ጠረጴዛ አይታሰብም። ለችግሮች መፍትሄ በሀይል ይገኝ ይመስል ከሰላማዊ ውይይት ይልቅ ጉልበትን መርጠው ተመሳሳይ አዙሪት ውስጥ የገቡ አገራት ጥቂት አይደሉም። በዚህም ወደ መፍረስ አልያም ወደ መዳከምና አቅም አልባ የመሆን ደረጃ ላይ የደረሱ አገራት አሉ። ኢትዮጵያ ግን ከዚህ በመሻገር የውይይት ዐውድ በማዘጋጀት ልጆቿ በችግሮቻቸው ላይ በአንድነት እንዲመክሩ ተግታ እየሠራች ነው። 

ኢትዮጵያዊያንም በአንድነት ተወያይተው ከልዩነቶቻቸው ይልቅ አንድ የሚያደርጓቸውን አጉልተው ለማውጣት ጫፍ ላይ ደርሰዋል። ሀገራዊ ምክክሩ ደግሞ በአንድ ሀገር ውስጥ ችግሮችን ከመፍታት ባለፈ በመንግስትና በሕዝብ መካከል መተማመንና ግልጽነትን ለመፍጠር ትልቅ አቅም እንዳለው ነው መምህር ንጉሴ የገለጹት።

እንደመምህሩ ገለጻ፤ ከውይይቱ እንደ ሀገር ፖሊሲ ሊቀረጽባቸው በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ መረጃዎችን በገብዓትነት ለመሰብሰብ ይቻላል። በምክክሩ በዋናነት የሰላምም ሆነ የግጭትን ውጤት የሚቀምሰውን ማኅበረሰብ ማሳተፍ ችግሮችን በጋራ የመፍታት ልምድ እንዲዳብር ያደርጋል። ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በዚህ ረገድ አካታች መርህን መከተሉ በዜጎች ውስጥ ጥሩ ተስፋ እንዲፈጠር አድርጓል። 

የሕዝብን ፍላጎት አዳምጦ ምላሽ የሚሰጥ አካልን ፊት ለፊት አስቀምጦ ምክክር መደረጉ ከውይይት ማግስት አዎንታዊ ምላሽ ለማግኘት ያስችላል። በሁሉም ዘንድ ተቀባይነቱ ከፍ ያለ መንግስት የመፍጠር ዕድልን ከማስፋት ባለፈ ልዩነትን የሚያሰፉ ችግሮችን ከስር መሠረቱ የመንቀል አጋጣሚን እንደሚያመጣ ነው መምህር ንጉሴ የገለጹት።

የምክክር ኮሚሽኑ ዜጎችን አንድ የሚያደርጉ ጉዳዮችን በማንጸባረቅ የጋራ እሴት የመገንባት ኃላፊነት ተጥሎበታል። ይህ እውን በሚሆነበት ጊዜ የእኔነት ስሜት ተመናምኖ የእኛነት የሚለመልምበት አስተሳሰብ በዜጎች ውስጥ ይሰርጻል ተብሎም ይጠበቃል። ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ዘላቂ ሰላም፣ አብሮነትና በጋራ ሀገር በአንድነት ተባብሮ መስራትና በፍቅር የመኖር እሴት እንዲለመልም ምክክሩ መሠረት ይጥላል።

የኢትዮጵያውያን እሴትና የኮሚሽኑ ቅቡልነት!

ኢትዮጵያውያን የሀሳብ ልዩነቶችን በምክክር መፍታት የሚያስችል ባህላዊ እሴት ያላቸው ሕዝቦች ናቸው። ምንም እንኳ ከቦታ ቦታ ቢለያይም እያንዳንዱ ብሔረሰብ ግጭት የሚያስወግድበት ባህላዊ ሥነ ሥርዓት አለው። የአፈጻጸሙ ሂደት ጉራማይሌ ሊሆን ቢችልም እንኳ የሰላም ግንባታ ሂደት መሠረቱ ውይይት ነው። ይሁንና ችግሮችን በውይይት የመፍታት ልምዳችን በዘመናት ሽግግር ውስጥ የመደብዘዝ ዕድል ገጥሞታል። ይሁንና ከማኅበረሰቡ ማንነት ውስጥ ጨርሶ ስላልጠፋ ይህ በጎ እሴት አሁን እየታየ ላለው የሰላም እጦት ሁነኛና አስተማማኝ መፍትሄ ስለሚያመጣ ምክክሩ ተቀባይነት አግኝቶ በተስፋ ሊጠበቅ ችሏል።

በሌላ በኩል የምክክር ኮሚሽኑ የሚፈጥረው ምቹ ሁኔታ ዜጎች ችግሮቻቸውን ተናግረው ሊደመጡ የሚችሉበት ሰፊ መድረክ በመሆኑ ከሕዝቡ ዘንድ አዎንታዊ ምላሽ አግኝቷል። መምህር እንዳለ  እንደሚሉት፤ ውይይት ለሰላም ግንባታ ብቸኛ አማራጭ ሲሆን፤ መንግስትም የሕዝብን ሀሳብ ለመስማት ዕድል ያገኛል። በእዚህም የምክክር ኮሚሽኑ ተቀባይነት መጉላቱን ነው የገለጹት።

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኢትዮጵያውያን በችግሮቻቸው ላይ መክረው ለመግባባት የሚያስችላቸው ነው። የውይይት መድረኩ አንዱ የሌላውን ችግር በመረዳት ሀገራዊ እይታውን የሚያሰፋበት መነጽር ይፈጥርለታል። ለመፍትሄ ከመነሳት በፊት ችግሮችን ማወቅ ይቀድማልና በምክክር ወቅት ኢትዮጵያ ምን መልክ እንዳላት ዋና ዋና ችግሮቿስ ምንድን ናቸው? የሚሉት በተወያዮች በኩል ይንጸባረቃሉ። 

የተወያዮች ኃላፊነት 

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሥራ ውጤታማነት በተወያዮች የሚወሰን ነው። ሁሉም ኢትዮጵያውያን በተለያዩ አደረጃጅቶች ሀሳቦቻችንን ያደርሱልናል ብለው የወከሏቸው ግለሰቦች አሉ። በመሆኑም እነዚህ የህብረተሰብ ተወካዮች ላለመግባባት ምክንያት የሆኑ ዋና ዋና ችግሮችን ለውይይት ይዞ ለመቅረብ ተገቢውን ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ይህን ሀሳብ የሚያንጸባርቁት በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሰቲ የታሪክ እና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር አጥናፉ ምትኩ ከማህበረሰብ ተወካዮች በሳል ሀሳብ ይዞ መቅረብ እንደሚጠበቅ ይገልጻሉ።

የግል ሀሳብን ሳይሆን የወከሏቸውን ህዝቦች ፍላጎትና አስተሳሰብ ማንጸባረቅ የተወያዮች ግዴታ ነው። በውይይት ወቅትም የራስን ብቻ ሳይሆን የሌሎችንም ሀሳብ የማድመጥ ባህልን አጉልቶ ማንጸባረቅ ይጠበቃል። በሌላ በኩል ተወያዮች ሀሳብ ከማመንጨት ጀምሮ የጋራ መፍትሄ የማፍለቅ ሃላፊነትም አለባቸው።

የመቻቻል እና የመከባበር ልምድ በውይይት ወቅት ጎልቶ እንዲወጣ ከማድረግ ባለፈ ወደ ማኅበረሰቡ ማዛመትም አስፈላጊ ነው። ያለፈውን በማንሳትና በመቆስቆስ አንዱ ሌላውን የሚከስ ሳይሆን ቁስሉን ለማከም መፍትሄ የሚፈልግ ስብዕናን መላበስ ያስፈልጋል። በእዚህ መንፈስ ለውይይት ከቀረብን ለዘመናት ሳያግባቡን የቆዩ ችግሮችን ፈትቶ እንደ ሀገር ለመሻገር አቅም መፍጠር ይቻላል።

የዜጎች ድርሻ

ተስፋ የነገ ብርሃን ጮራ ነው፤ ነገን የመመልከት መነጽር። ተስፋ ስኬታማ የሚሆነው ደግሞ ዛሬ በሚሠራው ሥራ ነው። እንጀራ ተጋግሮ ከመበላቱ በፊት ጤፍ ተፈጭቶ መቦካት አለበት። እንጀራ የመብላት ተስፋ ጤፍ ከመዝራት ጀምሮ የማስፈጨትና የማቡካት ሂደትን ይጠይቃል። የምክክር ኮሚሽን ፍሬያማ ውጤት በቅድመ ዝግጅት ምዕራፉ የጠራ ግንዛቤ መያዝና ቀና አመለካከት መላበስን ይጠይቃል። ይሆናል፤ ይሳካል ብሎ አዎንታዊ እንቅስቃሴ ማድረግና ከአላስፈላጊ ትችት መራቅም እንዲሁ።

መምህር አጥናፉ እንዳሉት የምክክር ኮሚሽኑ ዓላማ ግቡን እንዲመታ በተለይ የአገር ሽማግሌዎች አገር በቀል እውቀቶችን በማቀበል፤ ምሁራን የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ በመቀመር እና የምርምር ሥራዎችን በማቅረብ የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል። አካታችነቱን ተጠቅመው ሀሳብ ለማዋጣትና ለመደገፍ ለዜጎች የተሰጠ እድል በመሆኑ በአገባቡ በመጠቀም ተባብሮ እውን ማድረግ ይገባል።

ኢትዮጵያ ብሩህ የአብሮነትና የሰላም ተስፋን በምክክር ኮሚሽኑ ላይ የመጣሏ ምሥጢር የቤት ገበናን በቤት ውስጥ መፍታት የሚችል ቁልፍ ይዞ ስለተነሳ ነው። ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ሀገር በቀል እውቀቶችን ተንተርሶ ከባዳ ዐይንና ጆሮ የራቀ ሁነኛ መፍትሄን እንካችሁ እያለ ነው። ዜጎችም ለመቀበል እጃቸውን ዘርግተው በመጠባበቅ ላይ ናቸው። ይሄን ደግሞ በየአካባቢው ለኮሚሽኑ እየተደረገ ያለው የህዝብ አቀባበልና ድጋፍ ያረጋግጣል። 

ኮሚሽኑ አሁን የቀረውን የቅድመ ውይይት ሂደት ጨርሶ ወደዋናው ምክክር ሲገባ ከአንደበት ይልቅ ለጆሮ ቦታ ሰጥቶ በሰከነ መንፈስ ውይይቱን የማስኬድ ኃላፊነት መሸከም ከሁሉም ይጠበቃል። ሰላም !!! 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም