ቀጥታ፡

የሃላላ ኬላ ሪዞርት እና የዝሆን ዳና ሎጅ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት እንዲሰጡ በአግባቡ እናስተዳድራለን

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 5/2016(ኢዜአ)፦  በኢትዮጵያ ስካይ ላይት ሆቴል ስር የሚያስተዳድራቸውን የሃላላ ኬላ ሪዞርት እና የጨበራ ጩርጩራ ዝሆን ዳና ሎጅ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት እንዲሰጡ በአግባቡ እንደሚመራ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስታወቀ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት በገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች የተገነቡ ሎጅና ሪዞርቶች ለክልሎች ተላልፈው የኢትዮጵያ ስካይ ላይት ሆቴል እንዲያስተዳድራቸው የሚያደርግ ስምምነት ሚያዚያ 24/2016 ዓ.ም መፈረሙ ይታወቃል።

በዛሬው እለትም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) የጨበራ ጩርጩራ የዝሆን ዳና ሎጅና የሃላላ  ኬላ ሪዞርት የማስተዳደር ውልን ተፈራርመዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው በዚሁ ወቅት፣ አየር መንገዱ በረራ ከጀመረበት ወቅት አንስቶ የኢትዮጵያን የቱሪዝም መዳራሻዎችን ሲያስተዋወቅ መቆየቱን ገልጸዋል።


 

ከዚህም ባሻገር በሆቴል አገልግሎት ዘርፍ ባለ 5 ኮከብ የሆነውን የኢትዮጵያ ስካይ ላይት ሆቴል ተገንብቶ ወደ ስራ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት  እየሰጠ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

አየር መንገዱ በገበታ ለሀገር የተገነቡ ሎጅና ሪዞርቶችን በስካይ ላይት ሆቴል ስር እንዲያስተዳድር መደረጉ የሆቴል ኢንዱስትሪውን ለማስፋፋት ምቹ መደላድል እንደፈጠረለት አስረድተዋል።

በዛሬው ዕለትም የጨበራ ጩርጩራ የዝሆን ዳና ሎጅና የሃላላ ኬላ ሪዞርትን በኢትዮጵያ ስካይ ላይት ሆቴል ስር በሚጠበቀው የጥራት ደረጃ ለማስተዳደር ውል መፈራረማችን ትልቅ ዕድል ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቱሪዝም መስኩን ለማስፋፋት በአየር ትራንስፖርት ዘርፉ የጀመራቸውን ስራዎች በሆቴል አገልግሎት ዘርፉም ለመድገም በከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።


 

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በበኩላቸው የኢትዮጵያ ስካይ ላይት ሆቴል በዘርፉ ያለው ልምድና ተሞክሮ ሪዞርትና ሎጆችን በብቃት እንደሚመራ የሚያስተማምን ነው ብለዋል።

በዚህም ወደ አካባቢው ለሚያቀኑ ጎብኝዎች ደረጃውን የጠበቀ የሆቴል አገልግሎት በመስጠት ከአካባቢው ባለፈ የኢትዮጵያን የቱሪዝም  ዘርፍ ይበልጥ እንደሚያሳድግ ተናግረዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም