በአፍሪካ በ2027 ለሁሉም ዜጋ የሚቲዎሮሎጂ ቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃዎች ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ በ2027 ለሁሉም ዜጋ የሚቲዎሮሎጂ ቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃዎች ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 5/2016(ኢዜአ)፦ በአፍሪካ እ.አ.አ በ2027 ለሁሉም ዜጋ የሚቲዎሮሎጂ ቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃዎችን ለተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የዓለም የሚቲዎሮሎጂ ድርጅት የአፍሪካ ቀጣና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት ለሶስት ቀናት የሚቆየውን የ19ኛ ዙር የመጀመሪያ አህጉራዊ ስብስባውን በበየነ መረብ በመታገዝ በአዲስ አበባ እያካሄደ ነው።
ይህንን አስመልክቶ የአፍሪካ ቀጣና የጽህፈት ቤቱ ዳሬክተርና የማህበሩ ፕሬዝዳንት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
የዓለም የሚቲዎሮሎጂ ድርጅት የአፍሪካ ቀጣና ማህበር ፕሬዝዳንት ፈጠነ ተሾመ ስብሰባው ዓለም አቀፍና ቀጣናዊ ትብብርን ማጠናከርን ያለመ ነው ብለዋል።
ዛሬን ጨምሮ ለተከታታይ ሶስት ቀናት በአህጉሩ የሚገኝን ሃብት በጋራ መጠቀም በአየር ሁኔታ መለዋወጥ ተጽእኖ የሚጎዱ አካባቢዎችን ታሳቢ ያደረጉ ውይይቶች ይደረጋሉ ነው ያሉት።
በአየር ሁኔታና አየር ጸባይ የተጋላጭነት መጠንን ለመቀነስ የትንበያ መረጃ መሰብሰቢያ ጣቢያ በመትከል፣ የሚቲዎሮሎጂ መረጃዎችን ለመሰብሰብ የሳተላይት መረጃዎችን ለመጠቀም የአገራትን አቅም ማሳደግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
አገራት የራሳቸውን ትንበያ የሚሰጡበትን አቅም በመፍጠር በትንበያው መሰረት የግብርና፣ የውሃ፣ የጤናና የአደጋ መከላከል ተቋማት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደርጋል ነው ያሉት።
የሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት ድንበር ተሻጋሪ በመሆኑ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ትብብርን በማጠናከር መስራት ወሳኝ መሆኑን በአፅንዖት አንስተዋል።
የዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት የአፍሪካ ቀጣና ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር አግነስ ኪጃዚ(ዶ/ር) በበኩላቸው በዚህ ስብሰባ ቀደም ሲል በተካሄዱ ስብሰባዎች የተላለፉ ውሳኔዎች ውጤታማነት እንደሚገመገም ገልጸዋል።
በአህጉሩ በዘርፉ የተያዙ እቅዶች፣ በቀጣይ ትኩረት የሚደረግባቸው ጉዳዮች፣ የመሰረተ ልማት ችግር በመፍታትና ሌሎች ጉዳዮች ላይ በትኩረት ይመከራል ብለዋል።
እ.አ.አ በ2027 ሁሉም የዓለም ህዝብ የአየር ትንበያ የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃ እንዲያገኝ ለማስቻል የተያዘውን እቅድ በአፍሪካም እውን ለማድረግ አቅም ማሳደግ ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
የዓለም የሚቲዎሮሎጂ ድርጅት ከአየር ጸባይ፣ ከውሃ፣ ከአካባቢ እንዲሁም ከአየር ሁኔታ ጋር ተያያዥነት ባላቸው ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ድርጅት ነው።
ድርጅቱ በተለያዩ አህጉራት ካሉት ጽህፈት ቤቶች ውስጥ የአፍሪካ ቢሮው የሚገኘው በአዲስ አበባ ነው።