ቀጥታ፡

በለውጡ አመታት የቴክኖሎጂ፣ የጥራት የአሰራር ስርዓትና ሌሎችም ማሻሻያዎች ተደርገዋል- የምግብና መድኃኒት ባለስልጣን

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 5/2016(ኢዜአ)፦ በለውጡ አመታት የቴክኖሎጂ፣ የጥራት የአሰራር ስርዓትና ሌሎችም የአሰራር ማሻሻያዎች መደረጋቸውን የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ገለጸ።

የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ከፕሮሞቲንግ ኳሊቲ ኦፍ ሜዲሲንስ ፕላስ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የምክክር መድረክ በዋነኝነት ሃብት ለማሰባሰብና ድጋፍ ለማድረግ የሚያግዝ መሆኑ ተመላክቷል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሄራን ገርባ፤ በባለፉት አምስት አመታት በተቋሙ የተለያዩ የለውጥ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

ከለውጥ ስራዎቹ መካከልም የህግ ማዕቀፍ፣ የአደረጃጀት፣ የመሰረተ ልማትና የቴክኖሎጂ ማሻሻያ እንዲሁም የጥራት የአሰራር ስርዓት መዘርጋት መሆኑን ጠቅሰዋል።


 

በእስካሁኑ ሂደት አጋር ድርጅቶች የፋይናንስና የአቅም ግንባታ ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውንም አንስተዋል።

የመድኃኒት ጥራት ምርመራ፣ የህክምና ጓንት፣ የምግብ፣ የመድኃኒት ኢንስፔክሽንና ሌሎች ላቦራቶሪዎች እውቅና ማግኘታቸውን ጠቅሰዋል።

በቀጣይም አስር አመትም በአፍሪካ የልህቀት ማዕከል ለመሆን እቅድ ይዞ እየሰራ መሆኑን ገልጸው ለስኬቱ የአጋር አካላት የተጠናከረ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

በአሜሪካ የተራድኦ ድርጅት የሚደገፈው የፕሮሞቲንግ ኳሊቲ ኦፍ ሜዲሲንስ ፕላስ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዘላለም ማሞ፤ ድርጅቱ ባለፉት 15 አመታት በተለይም አቅም ግንባታ ላይ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸዋል። 

ከባለስልጣኑና የክልል ተቆጣጣሪ አካላት በተጨማሪ በአገሪቱ ያሉ የአገር ውስጥ መድኃኒት ፋብሪካዎች የቴክኒክ ድጋፍ ማድረጉንም አስታውሰዋል።

  

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም