አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ሥራዎችን ለማስፋት የሚያከናውናቸው ተግባራት ተጠናክረው ቀጥለዋል - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ሥራዎችን ለማስፋት የሚያከናውናቸው ተግባራት ተጠናክረው ቀጥለዋል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 5/2016(ኢዜአ)፦ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ሥራዎችን ለማስፋትና ከተለያዩ አካላት ጋር ያለውን ትብብር ለማጠናከር የሚያከናውናቸው ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸውን ገለጸ።
ዩኒቨርሲቲው "የ2024 ዓመታዊ የምርምር፣ የቴክኖሎጂና የጆፕ-ፌር" አውደ ርዕይ ዛሬ ተከፍቷል።
አውደ ርዕይው ዛሬን ጨምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ሲሆን በተለያዩ መምህራንና ተማሪዎች የተሰሩ የምርምር ውጤቶች ይቀርባሉ ተብሏል።
አውደ ርዕዩ አዳዲስ ተመራቂዎች ከወደፊት ቀጣሪ ተቋማት ጋር የሚገናኙበት መድረክ እንደሚሆንም ተገልጿል።
የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሳሙዔል ክፍሌ(ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ዩኒቨርሲቲው ወቅቱ በሚጠይቀው ልክ ለማደራጀት የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎች እየተሰሩ ነው።
የሪፎርሙ ዋና አለማም ዩኒቨርሲቲውን ራስ ገዝ ከማድረግ ባለፈ በአፍሪካ ግንባር ቀደም የምርምር፣ የቴክኖሎጂና የልሕቀት ማዕከል ለማድረግ ያለመ መሆኑንም ነው ያስረዱት።
በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ዩኒቨርሲቲው ተግባራዊ በሚያደርገው ስትራቴጂክ እቅድም ለጥናት፣ ምርምርና ለቴክኖሎጂ ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት መሰጠቱን አንስተዋል።
ይህንንም ተከትሎ ዩኒቨርስቲውን ምቹ የምርምር ማዕከል ለማድረግና ከተለያዩ አካላት ጋር ውጤታማ አጋርነት ለማጠናከር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና በበኩላቸው በተለያዩ መስኮች ውጤታማ ሥራዎችን ለማከናውን በቴክኖሎጂ የተደገፉ ተግባራትን ማከናወን ተገቢ ነው ብለዋል።
አገራት ካለባቸው ሁለንተናዊ ችግሮች በፍጥነት ለመላቀቅ የፈጠራ ሥራ ላይ ማተኮር ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ጠቁመው በተለይም ለዘላቂ ልማት በቴክኖሎጂ የታገዙ መፍትሄዎች ወሳኝ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በዚህ ረገድ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እያደረገ ያለው ተግባር የሚበረታታ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ኢንስቲትዩቱ ለስኬታማነቱ ሁለተናዊ ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።