አምራች ኢንዱስትሪዎች በማዕድን ዘርፍ በመሰማራት የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ አቅም ማሳደግ ይገባቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
አምራች ኢንዱስትሪዎች በማዕድን ዘርፍ በመሰማራት የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ አቅም ማሳደግ ይገባቸዋል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 5/2016(ኢዜአ)፦ አምራች ኢንዱስትሪዎች በማዕድን ዘርፍ በመሰማራት የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ አቅም እንዲያሳድጉ የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጂነር ሐብታሙ ተገኝ ጥሪ አቀረቡ።
ከኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ጎን ለጎን ከሚካሄዱ መርኃ-ግብሮች መካከል "የግል ኢንቨስትመንት እና አስቻይ ሁኔታዎች" በሚል የፓናል ውይይት ተካሂዷል።
የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጂነር ሐብታሙ ተገኝ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ከውስን የኢኮኖሚ አምዶች ወደ ብዝኃ ኢኮኖሚ እየተንቀሳቀሰች ነው።
አንድን ሀገር አምራች ከሚያስብሉ ዘርፎች መካከል አንዱ የማዕድን ዘርፍ መሆኑን አንስተዋል።
እንደ ሀገር ተወዳዳሪ መሆን የሚቻለው የማዕድን ጥሬ ዕቃዎች በሀገር ውስጥ አምርቶና እሴት ጨምሮ መጠቀም ሲቻል መሆኑን አመላክተዋል።
ከዚህ አኳያ ውስን ጅምሮች ብቻ መኖራቸውን ገልጸው፤ በሲሚንቶ እንዲሁም በጣም በትንሹ ወርቅ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ሁሉም ነገር በውስጧ የያዘች ሐብታም መሆኗን እና ለብረት፣ ለማዳበሪያ፣ ለአረንጓዴ ኃይል እንዲሁም ለመድኃኒት የሚውሉ ውጤቶች ለማምረት ትኩረት መሰጠቱን ጠቁመዋል።
አሁን ባለው ሁኔታ እሴት ያልተጨመረባቸው የማዕድን ውጤቶች ለውጭ ገበያ እየቀረቡ ሲሆን፤ ስታርትአፖችን በማሳተፍ አጠቃላይ የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት ከባቢ ለማሻሻል እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይም እነዚህ እሴት ያልተጨመረባቸውን ምርቶች መቀነስ በዘርፉ የተሰጠው አቅጣጫ መሆኑን ጠቁመዋል።
ዘርፉ በማኑፋክቸሪንግ፣ በግብርና እንዲሁም በአጠቃላይ ኢኮኖሚውን በሚደግፍ አካሄድ እየተመራ መሆኑን አመላክተዋል።
አምራች ኢንዱስትሪዎች በማዕድን ዘርፍ በመሰማራት የኢትዮጵያን ኢንዱስትራላይዜሽን(አምራችነት) ማረጋገጥ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ኢንዱስትሪዎቹ ይህንን ተግባራዊ ካደረጉ ጥሬ ዕቃ ፍለጋ ወደ ሌላ ቦታ እንደማያማትሩ አመላክተዋል።
ዘርፉ ከፍተኛ ካፒታል የሚጠይቅ ቢሆንም በጋራ ማልማት እንደሚገባ ገልጸው፤ ከውጭ የሚገቡ ጥሬ ዕቃዎችን በሀገር ውስጥ መተካት ከኤክስፖርት የማይተናነስ መሆኑን ገልፀዋል።
መንግሥት ለአምራች እና ማዕድን ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱን ገልጸው፤ ቀጣይ ጊዜያት ብሩህ መሆናቸውንም አመላክተዋል።