የሞጆ ወደብና ተርሚናልን የዲጂታል አሠራር በማስፋት አገልግሎት አሰጣጡን ይበልጥ የተቀላጠፈ ማድረግ ይገባል- ቋሚ ኮሚቴው - ኢዜአ አማርኛ
የሞጆ ወደብና ተርሚናልን የዲጂታል አሠራር በማስፋት አገልግሎት አሰጣጡን ይበልጥ የተቀላጠፈ ማድረግ ይገባል- ቋሚ ኮሚቴው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 5/2016(ኢዜአ)፦ የሞጆ ወደብና ተርሚናልን የዲጂታል አሠራር በማስፋት አገልግሎት አሰጣጡን ይበልጥ የተቀላጠፈ ማድረግ እንደሚገባ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።
የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ አባላት በኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ በሞጆ ወደብና ተርሚናል የመስክ ምልከታ አድርገዋል።
በቆይታቸውም የባቡር እና የኮንቴይነር ተርሚናል፣ ሜጋ መጋዘን እና በወደቡ ያሉ የተለያዩ መሠረተ- ልማቶችን ጎብኝተዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ መሐመድ አብዶ (ዶ/ር) በመስክ ምልከታው ጥሩ ክንውን የተመለከቱባቸው አሠራሮች መዘርጋታቸውን ገልፀዋል።
የአሠራር ሂደቱን የተቀላጠፈ ለማድረግና ትርፋማነቱን አስቀጥሎ ለመዝለቅ እያደረገ ያለው ጥረትም የሚበረታታ ነው ብለዋል።
በመሆኑም የዲጂታል አሠራሩን በማስፋት አገልግሎት አሰጣጡን ይበልጥ ቀልጣፋ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ አመላክተዋል።
የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ የኮርፖሬት አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወንድሙ ደንቡ፤ ከቋሚ ኮሚቴው የመስክ ምልከታ ጠቃሚ ግብዓቶች መገኘታቸውን ተናግረዋል።
በመሆኑም በቀጣይ ተጠናክረው መቀጠል ያለባቸውን ሥራዎች በማስቀጠል ተጨማሪ ሥራ የሚጠይቁ ላይ በማተኮር የሚሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
የሞጆ ወደብና ተርሚናል ከ80 በመቶ በላይ የገቢ ወጪ ንግድ የሚከናወንበት መሆኑ ይታወቃል።