መንግስት በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለአምራች ኢንዱስትሪው የሰጠው ትኩረት ከፍተኛ ለውጥ አምጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለአምራች ኢንዱስትሪው የሰጠው ትኩረት ከፍተኛ ለውጥ አምጥቷል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 5/2016(ኢዜአ)፦ መንግስት በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለአምራች ኢንዱስትሪው የሰጠው ትኩረት ምርታማነትን በማሳደግ ከፍተኛ ለውጥ ማመጣቱን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሚሊኒየም አዳራሽ የተዘጋጀውን ኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ባሳለፍነው ሳምንት ማስጀመራቸው ይታወቃል፡፡
ኤክስፖውን የጎበኙት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ፥ መንግስት የአምራች ኢንዱስትሪው ላይ እመርታዊ ለውጥ ያመጡ የፖሊሲ እርምጃዎችን እየወሰደ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ኢንዱስትሪዎች ያሉባቸውን የግብዓትና የፋይናንስ እጥረት የመፍታት፣ የገበያ ትስስርን የማጠናከርና ዘርፉ ሰፊ የስራ ዕድል እንዲፈጥር ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ጠቅሰዋል።
በዚህም ከውጪ ሀገር የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ከመተካት አኳያ በምርት ዓይነትም ይሁን በገንዘብ መጠን ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ መዘጋጀቱ ህብረተሰቡ በሀገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶችን እንዲያውቅና እንዲጠቀም በማድረግ ረገድ ትልቅ ግንዛቤ የሚፈጥር ስለመሆኑ ገልጸዋል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት ለአምራች ኢንዱስትሪው በተሰጠው ትኩረት ዘርፉ ከሀገር ውስጥ ጥቅል ምርት ያለው ድርሻ ማደጉን ጠቁመው፥ ይህም ለኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግሩ ዓይነተኛ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመው የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት አምራቾች የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ በተሟላ መልኩ እንዲያደርጉም አሳስበዋል፡፡
በኤክስፖው ምርታቸውን ካቀረቡት መካከል የአዳማ ዴቨሎፕመንት ድርጅት ተወካይ ወይዘሮ አበራሽ ታደሠ ኤክስፖው ምርታቸውን ለማስተዋወቅና የገበያ ትስስር ለመፍጠር ትልቅ ሚና እንዳለው ገልጸዋል፡፡
የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ተወካይ ሚካኤል ደስታ በበኩላቸው ኤክስፖው ምርቶችን ከማሳየት ባሻገር የልምድ ልውውጥ ያደረጉበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኤክስፖው መዘጋጀት ዜጎች የሀገራቸውን ምርት እንዲያውቁና እንዲጠቀሙ ለማበረታታት አጋዥ መሆኑን የጠቀሱት የኢትዮጵያ የቤትና የቢሮ እቃዎች አምራቾች ማህበር ፕሬዚዳንት ትህትና ለገሰ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አምስት ቁልፍ የትኩረት አቅጣጫዎችን ይዞ በሚያዚያ 2014 ዓ.ም መጀመሩ ይታወቃል።
የሀገር ውስጥ ምርትና አምራቾችን ማጠናከር፣ መሪ ኢንዱስትሪዎችን መፍጠር፣ የኢንዱስትሪ ማህበረሰብ መገንባት፣ ጥናትና ምርምርን ማሳደግ እንዲሁም ምቹ የቢዝነስ ከባቢን መፍጠር ደግሞ ከንቅናቄው የትኩረት አቅጣጫዎች መካከል ናቸው።
መንግስት የተኪ ምርቶች ስትራቴጂ በማዘጋጀት እየሰራ ሲሆን 96 የሚሆኑ ምርቶችን በመለየት በሀገር ውስጥ ለመተካት እየሰራ ይገኛል።
ስትራቴጂው ተግባራዊ ከተደረገ ወዲህ የጸጥታ አካላትን የደንብ ልብስ እና የቢራ ብቅልን ጨምሮ አንዳንድ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ማምረት መጀመሩ ተጠቅሷል።
በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ከግንቦት 1/2016 ዓ.ም ጀምሮ ለአምስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ዛሬ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።