ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የጎንደር ከተማና አካባቢውን ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመሩ የውሃና መንገድ ፕሮጀክቶች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ መመሪያ ሰጡ - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የጎንደር ከተማና አካባቢውን ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመሩ የውሃና መንገድ ፕሮጀክቶች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ መመሪያ ሰጡ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 05/2016 (ኢዜአ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የጎንደር ከተማና አካባቢውን ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመሩ የውሃና መንገድ ፕሮጀክቶች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ መመሪያ ሰጡ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ መመሪያ የሰጡባቸው ፕሮጀክቶች የመገጭ ግድብ ፕሮጀክት፣ ጎንደር የንጹህ መጠጥ ውሃ ጉድጓድ ቁፋሮና የአዘዞ ጎንደር አስፋልት መንገድ ፕሮጀክት ናቸው፡፡
ፕሮጀክቶቹን በሚመለከትም የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ኢኒጂነር አይሻ መሀመድ፣የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢኒጂነር ሃብታሙ ኢተፋ እንዲሁም የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር መሃመድ አብዱረህማን የፕሮጀክቶቹን አፈፃፀም ሪፖርት አቅርበዋል፡፡
የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ኢኒጂነር አይሻ መሀመድ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ የመገጭ ግድብ ፕሮጀክት ያለ በቂ ጥናት ከረዥም ዓመታት በፊት መጀመሩን ጠቅሰዋል፡፡
በፕሮጀክቱ ግንባታ ሂደት ላይ ያጋጠመው አፈር መንሸራተትም አፈጻጸመሙን ወደ ኋላ እንዳጓተተው ገልጸው፤ ችግሩን በማስተካከል የግንባታ ስራው እተከናወነ መሆኑን ተናግርዋል፡፡
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ በበኩላቸው፤ የመገጭ ግድብ ፕሮጀክት እስኪጠናቀቅ ለከተማው ህዝብ ውሃ ማቅረብ የሚችሉ የሶስት ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ መከናወኑን አውስተዋል፡፡
ነገር ግን ከውሃ ማስተላለፊያ መስመር የዲዛይን ስራው በመጓተቱ ምክንያት አገልግሎት መስጠት እንዳልተቻለ ነው ተናገሩት፡፡
አሁን ላይ ከክልሉ መንግስት ጋር በመተባበር ችግሩን ለመቅረፍ እየተሰራ ስለመሆኑም ነው ያብራሩት።
የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር መሃመድ አብዱረህማን፤ አዘዞ ጎንደር መንገድ ግንባታ አፈፃፀም 60 ነጥብ 8 በመቶ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ቀሪ ስራዎችን በቀጣይ ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሀገራዊ ለውጡ በፊት ተጀምረው የቆሙ በርካታ የልማት ፕሮጀክቶችና የብድር እዳ ጫና ለውጡ መንግስት ወደ አመራርነት ሲመጣ ተቀበላቸው የኢኮኖሚ ስብራቶች መሆናቸውን ነው የተናገሩት፡፡
መንግስት በአንድ በኩል እዳ እየከፈለ በሌላ በኩል ደግሞ የቆሙ ፕሮጀክቶችን ለመቅረፍ በርካታ ስራዎችን እከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ከተጀመረ 15 ዓመታት ያስቆጠረው መገጭ ግድብ ፕሮጀክትም በዚሁ ማዕቀፍ የሚታይ መሆኑን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡
አመራሩም ይህን ከግንዛቤ ውስጥ በማሥገባት ይበልጥ መትጋት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡
በቀጣይ አቅም ያለው ተቋራጭን ወደ ስራ ከማስገባት ጀምሮ የመገጭ ግድብን በቅርብ ጊዜያት ውስጥ በማጠናቀቅ ህዝብን ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችሉ ስራዎች እንዲከናወኑ አስገንዝበው፤ መንግስት የሚጠበቅበትን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡
መንግስት የግድቡ ግንባታ ፕሮጀክትን በጥብቅ እንደሚከታተልም ተናግረዋል፡፡
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ከአማራ ክልል መንግስት ጋር በመተባበር የጥልቅ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶቹን በአጭር ጊዜ ውስጥ በማጠናቀቅ አገልግሎት እንዲያስጀምርም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ መመሪያ የሰጡት፡፡
በተመሳሳይ የአዘዞ ጎንደር አስፋልት መንገድ ፕሮጀክት ላይ የሚታዩ ችግሮች ተቀርፈው በአስቸኳይ እንዲጠናቀቅ አቅጣጫ ተቀምጧል።
ለፕሮጀክቶቹ መጠናቀቅ ህብረተሰቡ ከመንግስት ጎን በመቆም የሚጠበቅበትን ድጋፍ ምድርግ እንዳለብትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡