በከተማችን 597 የህጻናት መዋያዎች በመኖሪያ ቤቶች አካባቢ፣ በግል እና በመንግስት ተቋማት ውስጥ ተገንብተዋል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
በከተማችን 597 የህጻናት መዋያዎች በመኖሪያ ቤቶች አካባቢ፣ በግል እና በመንግስት ተቋማት ውስጥ ተገንብተዋል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 5/2016(ኢዜአ)፦ በከተማችን 597 የህጻናት መዋያዎችን በመኖሪያ ቤቶች አካባቢ፣ በግል እና በመንግስት ተቋማት ውስጥ ገንብተናል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት በዛሬው ውሏችን ከተለያዩ የአፍሪካ ሃገራት ልምድ ለመቅሰም ወደ መዲናችን ለመጡ መሪዎች የትውልድ ግንባታ ስራችን የሆነው የህጻናት መዋያዎችን እና ተያያዥ አገልግሎቶችን አስጎብኝተናል ብለዋል።
አክለውም ዛሬ አብዝተን የምንዘራው መልካም ዘር ነገ የተትረፈረፈ መልካም ፍሬን እንደሚሰጠን በማመን በከተማችን 597 የህጻናት መዋያዎችን በመኖሪያ ቤቶች አካባቢ፣ በግል እና በመንግስት ተቋማት ውስጥ ገንብተናል ብለዋል።
በእነዚህ ማቆያዎች ለህጻናቱ የተመጣጠነ ምግብ፣ የሞግዚት አገልግሎት፣ የጤና ክትትል፣ ትምህርት በጨዋታ መስጠት፣ የእናቶች ምክር አገልግሎት እንዲሁም ህፃናት የተሟላ እድገት እንዲኖራቸው ልዩ ክትትል ይደረግላቸዋል ሲሉም ገልጸዋል::
አዲስ አበባ ህጻናትን ለማሳደግ ምርጧ አፍሪካዊት ከተማ የማድረግ ስራችን እውቅናን አግኝቶ ለሌሎች ልምድ የሚያካፍልበት ደረጃ ላይ በመድረሱ ደስታ ይሰማናል ብለዋል ከንቲባዋ።
በቀጣይ የህጻናት መዋያዎችን 1000 የመጫወቻ ቦታዎችን ደግሞ 12 ሺሕ ለማድረስ በርትተን እንስራ ሲሉም ከንቲባ አዳነች መልዕክት አስተላልፈዋል።
ይህን መልካም ስራ እዚህ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ላስተባበራችሁ፣ ለመራችሁ እና በቅርበት ከእኛ ጋር ለሰራችሁ ሁሉ በከተማ አስተዳደሩ እና በነዋሪዎች ስም አመሰግናለሁ ብለዋል።