12ኛው የአፍሪካ አቪዬሽን ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
12ኛው የአፍሪካ አቪዬሽን ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀመረ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 5/2016(ኢዜአ)፦12ኛው የአፍሪካ አቪዬሽን የባለድርሻ አካላት ጉባኤ በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ነው ።
12ኛው የአፍሪካ አቪዬሽን የባለድርሻ አካላት ጉባኤ "የአፍሪካን አቪዬሽንን ከማስተሳሰር ባሻገር" በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
ጉባኤው ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ቀናት የሚቆይ ሲሆን የዘርፉ ተዋናዮች ለአህጉሪቱ የአቪዬሽን መስክ መጪው ጊዜ ይዞት በሚመጣው እድሎች፣ በአፍሪካ አየር ትራንስፖርት ደህንነትና ኦፕሬሽን እና መሰል ጉዳዮች ላይ ይመክራል ተብሏል ።
በጉባኤው የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) ፣የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው፣ የአፍሪካ አየር መንገዶች ማህበር /አፍራ/ ዋና ፀሃፊ አብዱራህማን በርቴ ፣በአፍሪካ የሚገኙ አየር መንገዶችን የሚመሩ ሃላፊዎች፣ ዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፓርት ማህበር /አያታ/የአውሮፕላን አምራቾችና የዘርፉ ባለሙያዎች ታድመዋል።
በጉባኤው መክፈቻ ላይ የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትሩ አለሙ ስሜ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት ፤ የአየር ትራንስፖርት ዘርፍ ዓለም አቀፍ ኢኮኖሚን ለማንቀሳቀስ ቁልፍ ሚና አለው።
"ኢትዮጵያም በተያያዘችው የኢኮኖሚ እድገት የአየር ትራንስፖርት መስክ የማይተካ ሚና እንዳለው እንገነዘባለን" ብለዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተያያዘውን እድገትና ሁሉን አቀፍ የአቪዬሽን መስክ የሸግግር ልህቀት ለማረጋገጥ መንግስት የበኩሉን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው፣አየር መንገዱ የአፍሪካ አህጉርና የተቀረውን ዓለም በአየር ትራንስፖርት የማስተሳሰር ጉዞውን ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የያዘውን እቅድ እያሳካ ነው ብለዋል።
የአፍሪካን አገራትም የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር አየር መንገዶቹ ተቀራርበው መስራት እንደሚገባቸው ገልጸዋል።
መጪው ጊዜ የአየር ትራንስፖርት በአህጉሪቱ በይበልጥ የሚፈለግበት በመሆኑም ከወዲሁ በሰው ሃይልና ዘርፉ በሚጠይቀው ሁሉ መዘጋጀት ያስፈልጋል ብለዋል።
የአፍሪካ አየር መንገዶች ማህበር /አፍራ/ ዋና ፀሃፊ አብዱራህማን በርቴ ፣ጉባኤው የአፍሪካን የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ተግዳሮትና ያሉ እድሎችን ለመመልከት የሚያስችል ነው ብለዋል።